ቀጥታ፡

የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሉዓላዊነታችን ዘብ በመሆኑ ከጎኑ እንቆማለን-የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪዎች

ደብረ ማርቆስ፤ ጥቅምት 12/2019 (ኢዜአ)፦የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሰላምን በማፅናት የሀገርን ዳር ድንበር እያስከበረ ያለ የሉዓላዊነታችን ዘብ በመሆኑ ከጎኑ እንቆማለን ሲሉ የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ።

የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪዎች የመከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎች ሰላምን በማስከበር ሀገርን ለማጽናት እያደረጉ ያለውን ጥረት የሚደግፍ ህዝባዊ ሰልፍ አካሄደዋል።


 

በወቅቱም ነዋሪዎቹ እንደገለፁት፤ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሰላምን በማፅናት የሀገርን ዳር ድንበር እያስከበረ ያለ የሉዓላዊነታችን ዘብ በመሆኑ ከጎኑ በመሰለፍ  እንደግፈዋለን።


 

በድጋፍ ሰልፉ ከተሳተፉት ነዋሪዎች መካከል አቶ አንዱአምላክ ታመን፤ የሀገርን ደህንነት እና ነጻነት ለመጠበቅ ውድ ህይወቱን ለሚከፍለው የመከላከያ ሰራዊት ምስጋና ለማቅረብ በሰልፉ ላይ መሳተፋቸውን ገልፀዋል።

ሠራዊቱ የሀገርን ሰላምና ደህንነት ለማስከበር በዱር በገደሉ ከጠላት ጋር የሚዋደቅ በመሆኑ ለተግባሩ ምስጋናዬን በማቅረብ ከጎኑ በመሆን የድርሻዬን ለመወጣት ዝግጁ ነኝ ብለዋል። 

ወጣት መቅደስ ደርብ በበኩሏ፤ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ያላትን ድጋፍ ለመግለጽ ሰልፍ መውጣቷን ገልፃለች።


 

ሠራዊቱ ሰላምን በማፅናት የሀገርን ዳር ድንበር ለማስከበር ለሚከፍለው የህይወት መስዋዕትነት ክብር እንዳላት ገልፃ ከሠራዊቱ ጎን ለመቆም ዝግጁ መሆኗን አረጋግጣለች።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት የህዝቡን ሰላም ለማስጠበቅ እየከፈለ ያለውን ዋጋ በመገንዘብ በሰልፉ መሳተፋቸውን የገለፁት ደግሞ ሌላው የሰልፉ ተሳታፊ አቶ በእውቀት አታላይ ናቸው።


 

የከተማዋ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ መልካሙ ሽባባው በሰልፉ ላይ ባስተላለፉት መልእክት፤ የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና ሌሎች የጸጥታ አካላት ሀገርን ለማጽናት እያደረጉት ያለውን ጥረት ህዝቡ መደገፉ ወቅታዊና ከዜጋ የሚጠበቅ ኃላፊነት መሆኑን ገልጸዋል።


 

ዛሬ የተደረገው ህዝባዊ ሰልፍም የአገራችንን ህልውናና ሉዓላዊነት ለመዳፈርና ሰላም ለማሳጣት የሚጥሩ ጸረ-ሰላም ሃይሎችን በማውገዝ፣ መከላከያ ሠራዊቱ እየወሰደ ያለውን እርምጃ ለመደገፍ ያለመ ነው ብለዋል።

ጽንፈኞችም በግጭትና በጦርነት የሚፈታ ችግር ባለመኖሩ መንግስት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው በልማት እንዲሳተፉ መልዕክት የተላለፈበት መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይም የመከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎች ሀገር ለማጽናትና የህዝብ ደህንነትን ለማስጠበቅ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሁሉ ህዝቡ ከጎናቸው በመቆም ደጀንነቱን እንደሚያረጋግጥም አሳይቷል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም