ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ያላት ስትራቴጂክ ሚና እና ተጽዕኖ እየጎለበተ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 12/2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ያላት ስትራቴጂካዊ ሚና እና ተጽዕኖ እየጎለበተ መሆኑን የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አብዱልዋሳ አብዱላሂ (ዶ/ር) ገለጹ።

ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ


 

"ሕብረት ወይስ ክህደት? ፀረ-ኢትዮጵያ ጥምረት ከየት ወዴት?" በሚል መሪ ሀሳብ በኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ኮሌጅ እና በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት በጋራ የተዘጋጀ የፖሊሲ ውይይት እየተካሄደ ይገኛል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አብዱልዋሳ አብዱላሂ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት ፤ ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን ስትራቴጂካዊ ሚና በማጠናከር ላይ መሆኗን አንስተዋል።


 

ይህንንም ለማስቀጠል የሀገር ውስጥ አንድነትን በጋራ ጥቅም፣ በመከባበርና በዘላቂ ሀገራዊ ራዕይ ላይ መመሥረት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

የሀገር ውስጥ ልዩነቶችን በሰላማዊ፣ በፖለቲካዊና በዴሞክራሲያዊ መንገዶች መፍታት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የሀገር ውስጥ ችግሮችን ለመፍታት በውጭ ኃይሎች ወይም በተወካይ ጦርነቶች ላይ መመርኮዝ የሀገርን ጥቅም እንደማያስጠብቅ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የባሕር በር ጥቅሟን ለማስጠበቅም ከጎረቤት ሀገራት ጋር በውይይት፣ በስምምነትና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ በመመሥረት እየሰራች እንደምትገኝ ገልጸዋል።

በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታና በግብርና፣ በመሠረተ ልማት፣ በከተማ ልማትና በቴክኖሎጂ ዘርፎች የተከናወኑ ሥራዎች የጋራ ሀገራዊ ጥረት ውጤቶች መሆናቸውን አብራርተዋል።

እነዚህን ውጤቶች ማስቀጠል ለሀገሪቱ ስትራቴጂካዊ አቅም መጠናከር ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።

የመከላከያ ኢንስፔክተር ጄኔራል ቢሮ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ደሳለኝ ተሾመ በበኩላቸው፤ መድረኩ የኢትዮጵያን ሀገራዊ ጥቅም፣ ሉዓላዊነት፣ የቀጣናው ሚናና የሀገሪቱን ስትራቴጂካዊ ቀጣይነት በተመለከተ የፖሊሲ ውይይት ለማድረግ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ያላትን ስትራቴጂካዊ፣ ጂኦፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አቅም ለማጠናከርና በቀጣናው ያላትን ተጽዕኖ ለማሳደግ የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን አንስተዋል።

ሀገሪቱ ከውስጣዊ የታሪክ ተግዳሮቶችና ከውጫዊ የጂኦፖለቲካዊ ጫናዎች ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጉዳዮችን በስትራቴጂካዊ አመለካከት መመልከት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።


 

በተለይም ኢትዮጵያ የባሕር በር መዳረሻዋን ማጣቷና ከዚህ ጋር የተያያዙ የጂኦፖለቲካዊ ገደቦች በሀገሪቱ ስትራቴጂካዊ አቅም ላይ ያሳደሩትን ተጽዕኖ በጥልቀት መመርመር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ኮሌጅ ዋና አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል ጥላሁን ደምሴ በበኩላቸው፣ የሀገር ውስጥ ባንዳዎች ከውጭ ኃይሎች ጋር በመተባበር ችግሮችን ለመፍጠር የሚደረጉ ጥረቶች ለሀገራዊ አንድነትና ለቀጣናዊ መረጋጋት አደጋ እንደሚደቅኑ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያን ሀገረ መንግሥት ግንባታና ስትራቴጂካዊ አቅም ለማጠናከር በጋራ መመካከርና ዘላቂ መፍትሔዎችን ማፈላለግ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

በመድረኩ የቀጣናዊ ጂኦፖለቲካዊ ሁኔታዎች፣ የኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ ምላሽ፣ የኢትዮ-ኤርትራ ውጥረትና የደኅንነት ሁኔታዎችን የሚመለከቱ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ውይይት እንደሚደረግ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም