የሰው ሠራሽ አስተውሎት(ኤአይ) በሕክምና ምርመራ እና ውሳኔ አሰጣጥ ላይ አዲስ ምዕራፍ እየከፈተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሰው ሠራሽ አስተውሎት(ኤአይ) በሕክምና ምርመራ እና ውሳኔ አሰጣጥ ላይ አዲስ ምዕራፍ እየከፈተ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 12/2019 (ኢዜአ)፦ በጤናው ዘርፍ የሚደረጉ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ግኝቶች፣ በተለይም የሰው ሠራሽ አስተውሎት እመርታዎች፣ በሽታዎችን ቀድሞ በመመርመርና ትክክለኛ የሕክምና ውሳኔዎችን በመስጠት ረገድ አዲስ ምዕራፍ እየከፈቱ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።
ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ
የጤና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ የዓይን ሕክምና ባለሙያዎች ማህበር ጋር በመተባበር “የዓይን ህክምና አገልግሎትን በኢትዮጵያ ማሻሻል፡ ሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI)፣ ፈጠራ እና ተደራሽነት” በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጀው 26ኛው ዓመታዊ ሳይንሳዊ ጉባኤ እየተካሄደ ይገኛል።
በጤና ሚኒስቴር የሰው ሀብት ልማትና ማሻሻያ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አሰግድ ሳሙኤል በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) እና አዳዲስ ዲጂታል ቴክኖሎጂዎች የሕክምና ምርመራዎችንና አገልግሎቶችን ለማሻሻል ትልቅ ዕድል ይዘው መጥተዋል።
እነዚህ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች በገጠር አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች ጥራት ያለው የዓይን ሕክምና እንዲያገኙ ለማስቻል ጥቅም ላይ መዋል እንዳለባቸው ገልጸዋል።
አክለውም የዓይን ጤና ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ባለሙያዎች፣ ተመራማሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች እና የልማት አጋሮች የሚያደርጉት የተቀናጀ ጥረት ከፍተኛ ዋጋ ያለው መሆኑን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ የዓይን ሕክምና ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ማንደፍሮ ስንታየሁ በበኩላቸው፤ ጉባኤው ሳይንሳዊ እውቀቶችን ለመለዋወጥ፣ ልምድ ለመካፈል፣ የባለሙያዎችን ትስስር ለማጠናከር እና የሀገሪቱን የዓይን ሕክምና የወደፊት ዕጣ ፈንታ ለመቅረጽ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
ሰው ሠራሽ አስተውሎት በምርመራ እና በሕክምና ውሳኔ አሰጣጥ ላይ አዳዲስ ዕድሎችን የሚከፍት ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን ተናግረዋል።
ቴክኖሎጂን ብቻ መጠቀም በቂ ባለመሆኑ አዳዲስ ፈጠራዎችን ከሀገሪቱ እውነታ ጋር በማጣጣም በተለይም ለገጠሩ ማኅበረሰብ ጥራት ያለው የዓይን ጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።