ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የሚገኝበት ወታደራዊ ቁመና እና ግዳጅ የመፈፀም አቅም የሚያኮራ ነው

ደብረ ብርሃን፤ ጥቅምት 12/2019 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የሚገኝበት ወታደራዊ ቁመና እና ግዳጅ የመፈፀም አቅም የሚያኮራ መሆኑን የቀድሞ ሰራዊት አባላት ገለጹ።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በጀግንነቱና በሀገር ወዳድነቱ አልፎም በዓለም የሰላም አስከባሪነቱ ከፍ ያለ ስምና ዝና ያለው ሰራዊት መሆኑ ይታወቃል።

በመከላከያ ሰራዊት የተቋም ግንባታ ሂደት በዘመናት የመንግስት ለውጦች የተለያዩ ፈተናዎች ገጥመውት ቢያልፍም የሰራዊቱ ጀግንነትና ሀገር ወዳድነት ግን በማይናወጥ አቋም እንደቀጠለ ነው። 

በተለይም ደግሞ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የመከላከያ የተቋማት ግንባታና የሰራዊቱ ቁመና አስተማማኝ የሀገር መከታ መሆን አስችሏል።

በደብረ ብርሃን ከተማ ኢዜአ ያነጋገራቸው የቀድሞ ሰራዊት አባላት፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አሁን የሚገኝበት ወታደራዊ ቁመና እና ግዳጅ የመፈፀም አቅም የሚያኮራ መሆኑን ገልጸዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል አምሳ አለቃ ብርሃኑ ታደሰ፤ የሀገር መከላከያ ሰራዊት በየዘመናቱ ለሀገሩ መስዋእትነት በመክፈል በጀግንነት የተዋደቀና ለሀገሩ ብዙ ያበረከተ ባለውለታ መሆኑን ገልጸዋል።

ከጥንት ጀምሮ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ሰላም እንዳይኖራትና እድገቷ እንዲገታ በመጣር እስካሁንም መዝለቃቸውን አንስተው በፊትም ይሁን አሁን በሰራዊታችን ክንድ እየተመከተ ይገኛል ብለዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አሁን የሚገኝበት ወታደራዊ ቁመና እና ግዳጅ የመፈፀም አቅም የሚያኮራ መሆኑን አንስተው ለዚህ የሀገር ባለውለታ ሰራዊት ተገቢውን ክብርና ምስጋና መስጠት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

መቶ አለቃ ሰለሞን ዘለቀ፤ የኢትዮጵያ ክብርና ሉአላዊነት ተጠብቆ እስካሁን የዘለቀው በጀግኖች ልጆቿ ቆራጥ ትግልና መስዋእትነት መሆኑን ገልጸዋል።

የአሁኑ ሰራዊትም በላቀ ብቃትና ጀግንነት የሀገሩን ክብርና ሉአላዊነት በማስጠበቅ ለብሄራዊ ጥቅሟም መሳካት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በመሆኑም መከላከያ ሰራዊት አሁን የሚገኝበት ወታደራዊ ቁመና እና ግዳጅ የመፈፀም አቅም የሚያኮራ መሆኑን ተናግረዋል።

መቶ አለቃ ወንድወሰን ግዛው በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያን እድገትና ብልጽግና የማይቀበሉ ሃይሎችን ሴራ በማክሸፍ ረገድ የሰራዊቱን አደራና ሃላፊነት አድንቀው ወጣቶችም ይህንን አደራ መረከብ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የሀገር ጉዳይ ለአንድ አካል ብቻ የሚተው አይደለም ያሉት መቶ አለቃ ወንድወሰን፤ በታሪክ ቅብብሎሽ ሀገርን ማጽናት፣ ክብሯንና ሉአላዊነቷን አስጠብቆ መቀጠል ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም