ቀጥታ፡

ዲጂታላይዜሽን የተፋጠነ አገልግሎት በመስጠት የሕዝብ አመኔታን ያተረፈ የዳኝነት ተቋም ለመገንባት እያስቻለ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 12/2019 (ኢዜአ)፦የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማሳደግና የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓቱን በማዘመን የህዝብ አመኔታን ያተረፈ የዳኝነት ተቋም ለመገንባት የሚያስችሉ ውጤታማ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ፉአድ ኪያር ገለጹ።

ባለፉት ዓመታት የሕዝብን የፍትህ ፍላጎት ለማሟላት የተከናወኑት ዘመናዊና የተቀላጠፉ ተግባራት በፍትህ ሥርዓቱ ላይ ተጨባጭና ተስፋ ሰጪ ለውጦችን እያመጡ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመደመር መንግሥት ምሥረታ ወቅት እንዳሉት፣ ኢትዮጵያን ለአዲሱ ዘመን ብቁ ለማድረግ የተጀመረው የዲጂታል ኢትዮጵያ ጉዞ ሀገሪቱ የዓለምን ፈጣን ለውጥ በብቃት እንድትወጣ ብቻ ሳይሆን የራሷን እድል በራሷ እንድትወስን ትልቅ አቅም ፈጥሮላታል።


 

በዲጂታል መድረኮች ግንባታ የሄደችበት ርቀት  ነገን ለመዋጀት አስተማማኝ እና ጠንካራ መሠረት መሆኑንም አረጋግጠዋል።

የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ፉአድ ኪያር ለኢዜአ እንዳሉት፣ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የዲጂታል አሠራርን ለማስፋፋት ባለፉት የስትራቴጂክ ዘመናት የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በዚህም የጉዳዮች አመዳደብ ግልጽ፣ ፍትሐዊና ከሰው ንክኪ ነፃ እንዲሆን የሚያስችል የዲጂታል ሥርዓት ተዘርግቶ ተግባራዊ መደረጉን አስረድተዋል።


 

በተጨማሪም የኤሌክትሮኒክስ ፋይሊንግ አሠራር በመጀመርና ምስክሮች በኦንላይን ምስክርነታቸውን የሚሰጡበትን ሁኔታ በማመቻቸት የፍርድ ቤቶችን ሥራ የማቀላጠፍ እንቅስቃሴ መከናወኑን አንስተዋል።

ለእነዚህ የዲጂታል አሠራር ማሻሻያዎች መሳካትም ፍርድ ቤቶችን በኔትወርክ የማስተሳሰር ፕሮጀክት መጠናቀቁን፣ የመረጃ ማዕከል መቋቋሙንና አስፈላጊ ሶፍትዌሮች መልማታቸውን ገልጸዋል።

ዲጂታላይዜሽን ቀልጣፋና የተፋጠነ አገልግሎት በመስጠት የሕዝብ አመኔታን ያተረፈ የዳኝነት ተቋም ለመገንባት እያስቻለ መሆኑንም ተናግረዋል።

የተከናወኑት የሪፎርም ሥራዎች የጉዳዮችን አፈጻጸም ከማፋጠን ባለፈ የዳኞችን አቅም ለመገንባት፣ የውሳኔዎችን ጥራት ለማሻሻልና የባለጉዳዮችን ፍላጎት በተሻለ ሁኔታ ለሟሟላት ማገዛቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይም የዲጂታል አሠራርን የበለጠ ማስፋፋትና ባለጉዳዮችን በአክብሮት የማስተናገድ ባህልን ማሳደግ ትኩረት የሚሰጠው  መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም