የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከሀገር አልፎ ለአፍሪካ ሰላም ዘብ የቆመ አስተማማኝ ኃይል ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከሀገር አልፎ ለአፍሪካ ሰላም ዘብ የቆመ አስተማማኝ ኃይል ነው
ቦንጋ፤ ጥቅምት 12/2019 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከሀገር አልፎ የሌሎች አገራትን ሰላም በማስከበር የሚታወቅ ብቁ እና ጀግና ሰራዊት በመሆኑ ተገቢውን ክብርና እውቅና መስጠት እንደሚገባ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ የመጨረሻ ምሽግ የሆነው የሀገር መከላከያ ሰራዊት በህዝባዊነቱ፣ በብቃቱ፣ በጀግንነቱና ተልእኮ በመፈፀም አቅሙ ይታወቃል።
የውስጥ ባንዳዎችና የውጭ ጠላቶች የኢትዮጵያን ክፉ በማሰብ ለጥፋት ብዙ እየለፉ ቢሆንም በጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ዳር ድንበሯ፣ ክብሯና ሉአላዊነቷ ተከብሮ ይገኛል።
በመሆኑም ለዚህ ጀግና ሰራዊት ተገቢውን ክብርና እውቅና መስጠት እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የሀገር ሉአላዊነትና ዳር ድንበርን ከማስከበር ባለፈ በተሰማራባቸው የሰላም ማስከበር ተልእኮዎችና ግዳጆች በላቀ ብቃቱ የተመሰከረለትና የተመሰገነ መሆኑን አንስተዋል።
የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከሀገር አልፎ የሌሎች አገራትን ሰላም በማስከበር የሚታወቅ፣ የሀገር ኩራትና የጀግንነት ምልክት መሆኑን ገልጸዋል።
የቀድሞ የሰራዊቱ አባል የሆኑት በዛብህ ቡሾ፤ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከጥንት እስካሁን የሀገር ባለውለታ ሆኖ በጀግንነት ውርስ የቀጠለ ጠንካራ ሰራዊት መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ብቃትና ጀግንነቱ የተመሰከረለት ከሀገር አልፎ ለአፍሪካ ሰላም ዘብ የቆመ አስተማማኝ ሃይል መሆኑን በማንሳት ለዚህ ሃይል ተገቢውን ክብርና እውቅና መስጠት ይገባል ብለዋል።
በዚህ ዘመን ደግሞ ዘመኑ በደረሰበት ልክ በቴክኖሎጂ የታገዘ ተቋም የገነባ በትጥቆችና ወታደራዊ አቅሞች በእጅጉ ያጎለበተ ሆኖ በመገኘቱ የሁላችንም ኩራት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በቦንጋ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ መምህር ሰለሞን ማሞ፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በሰላም አስከባሪነት በመሰማራት የተሰጠውን ግዳጅና ሃላፊነት በላቀ ብቃትና ጀግንነት በመወጣት በአለም ላይ ትልቅ ስምና ዝና ያለው መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከሀገር አልፎ አፍሪካዊያን የሚኮሩበት የድል አድራጊነትና የጀግንነት ተምሳሌት መሆኑን ገልጸዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ወጣት ወንድማገኝ ከበደ፣ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ለሀገሩ ክብርና ሉአላዊነት ለሰንደቁ ሲል የትኛውንም መስዋእትነት በጀግንነት የሚከፍል በመሆኑ አደራውን ማስቀጠል ይጠበቅብናል ብሏል።
የመከላከያ ሰራዊት ተቋማትን የመጎብኘት እድል እንደነበረው በማስታወስ በተመለከተው ሁሉ ትልቅ ክብርና ኩራት እንደተሰማውም ተናግሯል።
የቀድሞ ፖሊስ አባል የነበሩት ሻለቃ ታደለ ተረፈ፤ የሀገር መከላከያ ሰራዊት በሀገሩ ሉአላዊነትና ዳር ድንበር የማይደራደር፣ በጀግንነቱና በድል አድራጊነቱ የሚታወቅ ጀግና ሰራዊት መሆኑን ገልጸዋል።
የሰራዊቱ ቁመና በሁሉም መመዘኛዎች የላቀ ብቃት ላይ መድረሱ ደግሞ ለሁላችንም ኩራት ሆኗል ብለዋል።