የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሃዋሳ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአዳማ ከተማ ፣ የዕለቱ ተጠባቂ መርሐ ግብሮች - ኢዜአ አማርኛ
የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሃዋሳ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአዳማ ከተማ ፣ የዕለቱ ተጠባቂ መርሐ ግብሮች
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 12/2019 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሶስተኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ ተጀምሯል።
በዕለቱ አራት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ሃዋሳ ከተማ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ከሁለት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ያገኘው ሃዋሳ ከተማ በአንድ ነጥብ 16ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በስድስት ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው።
ጨዋታው ሃዋሳ ከተማ የመጀመሪያ ድሉን ለማስመዝገብ፣ ንግድ ባንክ በድል ጉዞው ለመቀጠል የሚያደርጉት ነው።
ሌላኛው መርሐ ግብር ቅዱስ ጊዮርጊስ እና አዳማ ከተማ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ያገናኛል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ በአንድ ነጥብ 14ኛ፣ አዳማ ከተማ በአራት ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዘዋል።
የ16 ጊዜ የሊጉ አሸናፊ የመጀመሪያ ድሉን ለማሳካት ወደ ሜዳ ይገባል።
በሁለተኛ ሳምንት ከሸገር ከተማ ጋር ያለ ግብ አቻ የተለያየው አዳማ ከተማ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል።
በሌሎች መርሐ ግብሮች አዲስ አዳጊው ጋሞ ጨንቻ ከመቻል ከቀኑ 10 ሰዓት በአርባምንጭ ዩንቨርሲቲ አባያ ካምፓስ ስታዲየም እና ወላይታ ድቻ ከባህር ዳር ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት በሀላባ ኢንተርናሽናል ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።