የኒውክሌር ቴክኖሎጂ ልማት ለኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞና የኃይል ዋስትና - ኢዜአ አማርኛ
የኒውክሌር ቴክኖሎጂ ልማት ለኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞና የኃይል ዋስትና
የኢትዮጵያ ኒውክሊየር ኃይል ኮሚሽን በጥቅምት ወር 2018 ዓ.ም በሚኒስትሮች ምክር ቤት 49ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ በጸደቀው ደንብ ቁጥር 575/2025 መሠረት የሀገሪቱን እያደገ የመጣውን የኃይል ፍላጎት በዘላቂነት ለማሟላት እና የላቁ የቴክኖሎጂ ዘርፎችን ማዘመንን ታሳቢ በማድረግ ተቋቋመ።
ተቋሙ የተቋቋመበት ዋና ዓላማና ግብ ብሔራዊ የኒውክሊየር ኃይል ልማት ፕሮግራምን በበላይነት ለመምራት፣ የኒውክሊየር መሰረተ ልማትን ለመገንባት እና ዓለም አቀፍ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ (IAEA) መስፈርቶችን ያሟላ ሰላማዊ፣ አስተማማኝና ደህንነቱ የተጠበቀ የኒውክሊየር ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በሀገሪቱ ማረጋገጥ ነው።
ይህ ታሪካዊ ምሥረታ ኢትዮጵያ ካላት ከፍተኛ እምቅ አቅምና የተፈጥሮ ሀብት ተነስታ፣ እነዚህን ፀጋዎች ወደ ተጨባጭ ልማት፣ የቴክኖሎጂ ዕድገት እና ወደ ጋራ ብልጽግና ለመለወጥ የጀመረችውን አዲስ የሽግግር ምዕራፍ ያበሰረ ነው።
ኮሚሽኑ የተቋቋመው ኢትዮጵያ የጀመረችውን ሁለንተናዊ የብልጽግና ጉዞ ለማገዝ አስተማማኝ እና ዘላቂ የኃይል አማራጭ እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ ምክንያት ነው።
ሀገሪቱ በታዳሽ ኃይል ላይ ሰፊ ኢንቨስትመንት እያደረገች ቢሆንም፣ የኢንዱስትሪ ልማቱ እና የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ፈጣን ዕድገት አስተማማኝና የመሠረታዊ ጭነት (baseload) የኃይል ምንጭን ይፈልጋል።
የኒውክሊየር ቴክኖሎጂ አቅርቦት ደግሞ የአየር ንብረት ተፅዕኖን የሚቋቋም፣ የኃይል ዋስትናን በአስተማማኝ ሁኔታ የሚያጠናክር እና ከታዳሽ የኃይል አማራጮች ጋር ተደምሮ ሀገራዊ ልማትን ወደ ላቀ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ስትራቴጂካዊ ምሰሶ ነው።
ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የሀገሪቱን የኒውክሊየር ዝግጁነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግሩ በርካታ ተግባራትን በስፋት አከናውኗል።
በዚሁ መሠረት የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማቀላጠፍና የባለሙያዎችን አቅም ለማሳደግ ከዓለም አቀፍ ስትራቴጂካዊ አጋሮች ጋር የሁለትዮሽ ስምምነቶችንና ፍኖተ-ካርታዎችን የማዘጋጀት ሥራዎችን በስኬት አከናውኗል።
ከዚህ በተጨማሪም፣ በዘርፉ ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራትና ሳይንሳዊ ምርምርን ለማስፋፋት ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ለወጣት ባለሙያዎች የውጭ ሀገር የማስተርስ ዲግሪ የትምህርት ዕድሎችን ማመቻቸቱን ጨምሮ፣ ህብረተሰቡንና ባለድርሻ አካላትን ያሳተፉ አገራዊና ቀጣናዊ የአቅም ግንባታ አውደ ጥናቶችን በተከታታይ አካሂዷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ኒውክሊየር ኃይል ኮሚሽን ዛሬ ጎብኝተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ ተቋም ለኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ የልማት ርዕይ ከፍተኛ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ አለው በማለት ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ እጅግ ከፍተኛ በሆነ እምቅ አቅሟ እና በተትረፈረፈ ተፈጥሯዊ ሀብቷ ለረጅም ጊዜ እንደምትታወቅ አስታውሰው፣አዲሱ ምዕራፍ ደግሞ እነዚህን ሀብቶች ወደ ተጨባጭ ልማት፣ የቴክኖሎጂ እድገት እና ወደ ጋራ ብልጽግና መለወጥ ላይ እንደሚያተኩር አጽንኦት ሰጥተዋል።
ኮሚሽኑ ለብሔራዊ የኒውክሊየር ኃይል ፕሮግራም አስፈላጊ የሆኑትን ተቋማዊ እና ቴክኒካዊ መሠረቶች በመጣል ይህንን ርዕይ ለማሳካት ስትራቴጂካዊ ሚና እንዳለው የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ብቁ የሰው ኃይል ማፍራት፣ ሳይንሳዊ ምርምርን ማስፋፋት እና የተቋሙን ዕውቀት ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ ወሳኝ ተግባራት መሆናቸውንና ይህም የኒውክሊየር ኃይል ልማት ሰላማዊ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ አስተማማኝ እና ዘላቂ በሆነ መንገድ በኃላፊነት ስሜት እንዲከወን እንደሚያደርግ አስገንዝበዋል።
አስተማማኝና ዘላቂ የኃይል አቅርቦት ለኢንዱስትሪ፣ ለማኑፋክቸሪንግ፣ ለዲጂታል መሠረተ ልማትና ለአጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ሽግግር ወሳኝ ሚና አለው።
የኒውክሊየር ቴክኖሎጂ ደግሞ የኃይል ዋስትናን በማጠናከር እየጨመረ ያለውን ፍላጎት ለማሟላት ትልቅ ዕድል የሚፈጥር ከመሆኑም በላይ፤ ከኃይል ምርት ባለፈ በጤና፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በአካባቢ ጥበቃ ዘርፎች ለሀገራዊ ልማትና ለቴክኖሎጂ አቅም ግንባታ ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታል።
በመሆኑም ብሔራዊ አቅምንና ልዩ ሙያዊ ብቃትን በቁርጠኝነት ማዳበር፤ የኢትዮጵያን የኒውክሊየር ኃይል ልማት ሰላማዊ፣ አስተማማኝ እና ዘላቂ በሆነ መንገድ በኃላፊነት ስሜት ለመምራት ዋነኛው ቁልፍ ነው።
ይህን ሀገራዊ ፕሮግራም ስኬታማ ማድረግ፣ የቴክኖሎጂ አቅምን በመገንባት የነገውን ትውልድ ተጠቃሚ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ፣ የሀገሪቱን ሁለንተናዊ የብልጽግና ጉዞ እና የረጅም ጊዜ የልማት ርዕይ በተጨባጭ የሚያረጋግጥ ታሪካዊና ወሳኝ የሽግግር ምዕራፍ ነው።