ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ አካላት ላይ ጠንካራ የሕግ እርምጃ ይወሰዳል-ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ አካላት ላይ ጠንካራ የሕግ እርምጃ ይወሰዳል-ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ ፤ጥቅምት 11/2019 (ኢዜአ)፦ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ አካላት ላይ ጠንካራ የሕግ እርምጃ እንደሚወሰድ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪን ለመቆጣጠር ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
በመዲናዋ በመሠረታዊ የዕለት ተዕለት ፍጆታዎችና በቤት ኪራይ ላይ እየታዩ ያሉ ምክንያታዊ ያልሆኑ የዋጋ ጭማሪዎችን ለመቆጣጠርና የዜጎችን የኑሮ ጫና ለማቃለል እየተወሰዱ ባሉ የአጭርና የረጅም ጊዜ መፍትሔዎች ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ሰፊ ውይይት መደረጉን አመልክተዋል።
በተደረገው ውይይት የሥጋ፣ የምግብ ዘይት፣ የዳቦ፣ የታሸገ ውኃና የቤት ኪራይ ዋጋዎች ላይ የሚታዩ ያልተገቡ ጭማሪዎች በዝርዝር መገምገማቸውን ከንቲባዋ ገልጸዋል።
ችግሩን ከመሠረቱ ለመፍታትና ፍትሐዊ የገበያ ሥርዓትን ለማረጋገጥም ከተማ አስተዳደሩ ዋና ዋና እርምጃዎችን እየወሰደ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ከተማ አስተዳደሩ እየወሰዳቸው ካሏቸው እርምጃዎች መካከል የመጀመሪያው የምርት አቅርቦትን ማሳደግ ሲሆን፣ የመሠረታዊ ፍጆታ ምርቶችን አቅርቦት በመጨመር የዋጋ መረጋጋትን ለማምጣትና ሸማቹ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ ሁኔታዎች እንደሚመቻቹ ተናግረዋል።
የገበያ ማዕከላትን ማስፋፋትና የደላላ ሰንሰለትን ማሳጠር ትኩረት የተሰጠው ሲሆን፣ አምራቾችንና ሸማቾችን በቀጥታ የሚያገናኙ የገበያ ማዕከላትን በከተማዋ መግቢያ በሮች ላይ በማቋቋም ምርቶች በቀጥታ ለሸማቾች እንዲቀርቡ እየተሠራ እንደሚገኝ ነው ከንቲባዋ የገለጹት።
ሕብረተሰቡም ከእነዚህ የገበያ ማዕከላት በመገበያየት የተመጣጣኝ ዋጋ አማራጮችን እንዲጠቀም ከንቲባዋ ጥሪ አቅርበዋል።
የሸማቾች ማኅበራት የምርት አቅርቦትና ጥራት እንዲያድግ ተጨማሪ 500 ሚሊዮን ብር የሚያዝ ተዘዋዋሪ ፈንድ (Revolving Fund) መመደቡን አመልክተዋል።
የእሑድ ገበያዎችን የማስፋት ስራ እንደሚከናወን የገፈለጹት ከንቲባዋ ሸማቾች መሠረታዊ የዕለት ተዕለት ፍጆታዎቻቸውን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ የእሑድ ገበያዎች እንደሚስፋፉና አቅርቦታቸውም እንደሚጠናከር ገልጸዋል።
የገበያ ሥርዓትን በሚጥሱና ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ አካላት ላይ የቁጥጥርና የሕግ ማስከበር ሥራው ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስገንዝበዋል።
የአከራይና የተከራይ ግንኙነት በሕግ፣ በውል ስምምነትና በጋራ ኃላፊነት መመራት እንዳለበት ጠቅሰዋል።
ዜጎች መብታቸውን በሕጋዊ መንገድ እንዲያስከብሩና የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በማስረጃ እንዲያቀርቡ የተበረታቱ ሲሆን፣ በተመሳሳይም ተደራሽና ተመጣጣኝ የመኖሪያ ቤት አቅርቦትን ማሳደግ እንደ ዘላቂ መፍትሔ እየተሠራበት እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በተደረገው ውይይትም የአቅርቦት ችግሮችን ከመሠረቱ በመፍታት፣ ፍትሐዊ የገበያ ሥርዓትን በማረጋገጥና ሕገወጥ የዋጋ ጭማሪዎችን በመቆጣጠር የዜጎችን የኑሮ ጫና ለመቀነስ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ ለመሥራት መተማመናቸው ተጠቅሷል።
ሕብረተሰቡ አስተዳደሩ ባመቻቻቸው የሸማቾች ማኅበራትና የእሑድ ገበያዎች በመገበያየት የኑሮ ወጪውን እንዲቀንስ ከንቲባዋ ጥሪ አቅርበዋል።
ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።
በተጨማሪም ዜጎች ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ወይም የገበያ ሕግ ጥሰት ሲያጋጥማቸው በቂ ማስረጃ በማቅረብ ለሚመለከተው የከተማ አስተዳደር አካል ሪፖርት እንዲያደርጉ፣ ከተረጋገጠ መረጃ ውጭ ወሬዎችን ከማሰራጨት እንዲቆጠቡና ፍትሐዊ የገበያ ሥርዓትን በጋራ እንዲደግፉ አሳስበው፤ የዜጎችን የኑሮ ጫና ማቃለልና ፍትሐዊ የገበያ ሥርዓትን ማረጋገጥ የጋራ ኃላፊነት መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል።