ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የመረጃ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥና አስተማማኝ የስታቲስቲክስ ስርዓት መገንባት የሚያስችል አቅም ገንብታለች 

አዲስ አበባ፣ጥቅምት 11/2019 (ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ የመረጃ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥና አስተማማኝ የስታቲስቲክስ ስርዓት መገንባት የሚያስችል አቅም መገንባቷን የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በከር ሻሌ (ዶ/ር) ገለጹ።

የአፍሪካ ስታቲስቲክስ ኮሚሽን 10ኛ ጉባኤና የተባበሩት መንግሥታት የጂኦስፓሻል መረጃ አስተዳደር ኮሚቴ ለአፍሪካ 12ኛ ጉባዔ የጋራ የመክፈቻ መድረክ ተካሂዷል።   

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በተካሄደው ጉባዔ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ፣ የኢሲኤ ዋና ጸሐፊ ክሌቨር ጋቴቴ ተገኝተዋል።     

በተጨማሪም ፖሊሲ አውጪዎች፣ የስታቲስቲክስ ባለሙያዎች፣ የልማት አጋሮችና የመረጃ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በከር ሻሌ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ ጉባዔው የአፍሪካን ነባራዊ ሁኔታ የሚመጥን የስታቲስቲክስ ስርዓት በመገንባት የአህጉሪቱን የልማት ውጥኖች ማሳካት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ይመክራል። 

ጉባዔው በኢትዮጵያ መካሄዱ የሀገሪቷን መልካም ገጽታ ለመገንባት፣ ኮንፈረንስ ቱሪዝምን ለማሳደግና ተጨማሪ የኢኮኖሚ ጥቅም ለማስገኘት ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለውም ተናግረዋል። 

በአሁኑ ወቅት የስታቲስቲክስ መረጃ መሰብሰቢያ መንገዶችን በማዘመን እንደ ብሔራዊ መታወቂያና የሰው ሰራሽ አስተውሎት የመሰሉ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም እንደሚገባ ተናግረዋል። 

እነዚህ ዘመናዊ አሰራሮች ፈጣን፣ አስተማማኝና ወቅታዊ የስታቲስቲክስ መረጃዎችን ለማግኘት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱም ገልጸዋል። 

ሀገራት የመረጃ ሉዓላዊነታቸውን በማስጠበቅ በራሳቸው አቅም የስታቲስቲክስ ልማት መርሃ ግብሮቻቸውን መምራት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያም ይህንን መርህ ተከትላ የመረጃ ሉዓላዊነቷን ለማስጠበቅ የሚያስችል ተግባር በማከናወን ላይ መሆኗን ጠቁመው፤ ለዚህም የሰው ሰራሽ አስተውሎት ኢንስቲትዩት በመገንባት አርአያነት ያለው ተግባር እየፈጸመች እንደምትገኝ ገልጸዋል።

የሀገሪቷ የስታቲስቲክስ ልማት ፕሮግራም በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁንና በዚህም መሰረት አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት ክለሳና ጥናት እየተካሄደ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ የጥናቱ ውጤትም በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም