በክልሉ የግብይት ሥርዓቱን በማዘመንና ሕገ ወጥ ንግድን በመከላከል ገበያን ለማረጋጋት የተጀመሩ ሥራዎች ይጠናከራሉ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የግብይት ሥርዓቱን በማዘመንና ሕገ ወጥ ንግድን በመከላከል ገበያን ለማረጋጋት የተጀመሩ ሥራዎች ይጠናከራሉ
ሚዛን አማን፣ ጥቅምት 11/2019 (ኢዜአ)፡-በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የግብይት ሥርዓቱን በማዘመንና ሕገ ወጥ ንግድን በመከላከል ገበያን ለማረጋጋት የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ ገለጸ።
ቢሮው የ2019 በጀት ዓመት የሦስት ወራት የተግባር አፈጻጸምና የቀጣይ ተግባራት አቅጣጫ ላይ ያተኮረ ምክክር በሚዛን አማን ከተማ እያካሄደ ነው።
የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ ሕይወት አሰግድ በዚህ ጊዜ እንደገለጹት፣ የግብይት ስርዓቱን በማዘመን በሕዝብ ኑሮ ላይ ለውጥ የሚያመጡ የንግድና ገበያ ልማት ሥራዎች ላይ በትኩረት መሥራት ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ ነው።
በዚህም የንግድ ሰንሰለት ላይ የሚስተዋሉ ሌብነትና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል በሁሉም የክልሉ መዋቅሮች ዲጂታል ሥርዓትን ለማስፋፋት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በክልሉ በህዝቡ ኑሮ እና የእለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ ጫና እያሳደረ ያለውን ኮንትሮባንድና ሕገ ወጥ የዋጋ ጭማሪን የመከላከል ተግባር ጊዜ የማይሰጠው መሆኑንም ተናግረዋል።
እንደ ሃላፊዋ ገለጻ፣ በንግድ እንቅስቃሴ ላይ የሚስተዋሉ ብልሹ አሠራሮችን የማረምና የገበያ መሠረተ ልማቶችን በማጠናከር ደህንነቱ የተጠበቀ የገበያ ሥርዓትን መፍጠር ትኩረት የተሰጠው ነው።
የቢሮው ምክትልና ገበያ ልማት ዘርፍ ኃላፊ ወይዘሮ አሰገደች ወልደየስ በበኩላቸው አንዳሉት የኑሮ ውድነት ጫናን ለመቀነስ እየተሰራበት ያለው አምራቹና ሸማቹ በቀጥታ የሚያገናኝ የቅዳሜና እሑድ ገበያን ለማስፋፋት እየተሠራ ነው።
በክልሉ አርሶ አደሩን ከሸማቹ ጋር በቀጥታ በመገናኘት በተመጣጣኝ ዋጋ ግብይት የሚካሄድባቸው 39 የገበያ ማዕከላት እንዳሉም ተናግረዋል።
ነባር የቅዳሜና የእሑድ ገበያ ማዕከላትን ደረጃ ወጥ ማድረግን ጨምሮ 17 አዳዲስ ማዕከላትን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ለማቋቋም መታቀዱን ጠቁመዋል።
የንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ የልማት ዕቅድ ዳይሬክተር አቶ ገረመው ቆጬ ባለፉት ሦስት ወራት ሕገ ወጥ ንግድን ለመቆጣጠር በተደረገው ጥረት የተገኘን ከ37 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ገንዘብ መንግሥት ገቢ መደረጉን ተናግረዋል።
ሕገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎች ለመካከል በተከናወኑ ስራዎችም ከ193 ሺህ ሊትር በላይ ነዳጅ በህገወጥ መንገድ ሲዘዋወር በቁጥጥር ስር መዋሉን ጠቁመዋል።