በቤንች ሸኮ ዞን የሕዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
በቤንች ሸኮ ዞን የሕዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ
ሚዛን አማን፣ጥቅምት 11/2019 (ኢዜአ)፡-በቤንች ሸኮ ዞን የሕዝብን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት በልዩ ትኩረትና ቁርጠኝነት እንደሚከናወኑ የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኮጁ በዳካች ዛሬ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ በጠቅላላ ምርጫ ከሕዝብ የተጣለባቸውን አደራና ኃላፊነት ለመወጣት በጊዜ የለም መንፈስ ወደተግባር መገባቱን ገልጸዋል።
በዞኑ ልማት፣ መልካም አስተዳደር መረጋገጥ እና ሰላምን አጠናክሮ ለማስቀጠል ህዝብን በማሳተፍ በተደመረ አቅም እንደሚሰራም አመልክተዋል።
የመልካም አስተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ህዝቡ በዞኑ ካነሳቸው ቅሬታዎች መካከል በዋናነት እንደሚጠቀሱ አስታውሰው፣ በዞኑ በአገልግሎት አሰጣጥ የሚስተዋልውን ችግር ለመፍታት ለዲጂታል ሥርዓት መስፋፋት ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል።
ለዚህም በአሁኑ ወቅት በዞኑ አገልግሎት እየሰጡ ካሉ ሁለት መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በተጨማሪ በተለያዩ ከተሞች ሦስት አዳዲስ የአገልግሎት ማዕከላት ሥራ እንደሚጀምሩ ጠቁመዋል።
የሕዝቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ መንግሥት የነደፋቸው ሀገራዊ ኢኒሼቲቮችን በዞኑ በማጠናከር የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ይሰራል ሲሉም ገልጸዋል።
የቤንች ሸኮ ዞን ቡናን ጨምሮ የፍራፍሬ፣ የቅመማ ቅመምና ሌሎች የግብርና ምርቶች በስፋት የሚመረቱበት መሆኑን የጠቆሙት ዋና አስተዳዳሪው፣ በዚህም የግብይት ሥርአቱን በማስተካከል የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማሳደግ መታቀዱን አመልክተዋል።
በተለይም በዞኑ የሚስተዋለውን የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ ለመግታት ሕዝቡን ያሳተፈ ክትትልና ቁጥጥር ከማድረግ ባለፈ ህግን የማስከበር ሥራ እንደሚሰራ ነው የገለጹት።
ግንባታቸው ያልተጠናቀቁ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ከማጠናቀቅ ጎን ለጎን አዳዲስ መሠረተ ልማቶችን በሕዝብ ተሳትፎ የመገንባት ዕቅድ መያዙንም አስታውቀዋል።