የህዝቡን የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት ለሚከናወኑ ተግባራት ስኬታማነት የድርሻችንን እንወጣለን - የምስራቅ ጉራጌ ዞን ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የህዝቡን የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት ለሚከናወኑ ተግባራት ስኬታማነት የድርሻችንን እንወጣለን - የምስራቅ ጉራጌ ዞን ነዋሪዎች
ቡታጅራ ፤ ጥቅምት 11/2019(ኢዜአ):- የህዝቡን የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት በመንግስት ለሚከናወኑ ተግባራት ስኬታማነት የድርሻቸውን እንደሚወጡ የምስራቅ ጉራጌ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ፡፡
"በመደመር መንግሥት፣ የሕዝብ ድምፅ፣ የጋራ ተሳትፎ፣ የጋራ ልማት!” በሚል መሪ ሀሳብ ህዝባዊ የምክክር መድረክ በምስራቅ ጉራጌ ዞን ቡታጅራ ከተማ ተካሂዷል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል ቀኝአዝማች ፀጋዬ ታቦር እንዳሉት መንግሥት የህዝብ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ታላላቅ የልማት ስራዎችን በከተማና በገጠር እያከናወነ በመምጣቱ ማህበረሰቡ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነቱን እያረጋገጠ ነው።
እነዚህ ተግባራት ቀጣይነት እንዲኖራቸው ዘላቂ ሰላምን ማስጠበቅ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራበት እንደሚገባ ጠቁመው ለዚህም ከነዋሪው የሚጠበቀውን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
ሌላዋ የምክክር መድረኩ ተሳታፊ ወይዘሮ ሉባባ ተሰማ በበኩላቸው ወቅቱ የህዝቡን የጋራ ተጠቃሚነት ለማስቀጠል በጋራና በአብሮነት የምንሰራበት ነው ብለዋል።
ጤናዉ የተጠበቀ አምራች ዜጋን ለመፍጠር የሚያስችል በርካታ የጤና አገልግሎት እቅዶች እየተተገበሩ እንደሚገኝ የተናገሩት ደግሞ የምክክሩ ተሳታፊ አቶ አዳነ አለሙ ናቸው።
ነዋሪዎቹ ከዘላቂ ሰላም በተጨማሪ የመንገድ፣ የጤናና የትምህርት አገልግሎቶችና ሌሎች የመሰረተ ልማት ጥያቄዎቻቸውን ለክልሉ ርእስ መስተዳደር አቅርበው ምላሽ አግኘተዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የትምጌታ አስራት (ዶ/ር) ከህዝብ ለቀረበላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ የህዝቦችን አብሮነት በማጠናከር ለዘላቂ ሰላም መጠበቅና ልማት መጠናከር ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል ብለዋል።
ዘላቂ ሰላምን የማስጠበቅና የማህበረሰቡን የልማት ጥያቄ ደረጃ በደረጃ በፍትሐዊነት የመመለስ ስራዉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች አልፎ አልፎ የሚከሰቱ የፀጥታ ችግሮችን ለመፍታት የህግ ማስከበር ስራዉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ዘላቂ ሰላምን በማስፈኑ ተግባር የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶችና መላው ህብረተሰብ በትብብር መስራት እንደሚጠበቅብትም አጽንኦት ሰጥተዋል ፡፡
በመርሐ ግብሩ የክልል፣ የዞን፣ የወረዳና የቡታጅራ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮችና ከሁሉም መዋቅር የተለያዩ የማህበረሰብ ተወካዮች ተሳትፈዋል።