ቀጥታ፡

የምሉዕ ሉዓላዊነት ጉዞ- የኢትዮጵያ የአይበገሬነት ምስጢር

ኢትዮጵያ በዓለም ታሪክ ውስጥ የነፃነት፣ የጽናት እና የሰው ልጅ ኩራት ሆና የምትጠራ ታላቅ ሀገር ናት። የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደቷ አልጋ በአልጋ ሳይሆን በበርካታ ውጣ ውረዶች፣ ዘመናትን በተሻገሩ መገፋቶች እና የውጭና የውስጥ ጫናዎች ያለፈ ነው። ነገር ግን በእነዚህ ሁሉ ፈተናዎች ውስጥ ያለፈው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ሀገራዊ ሉዓላዊነቱን እና የግዛት አንድነቱን አሳልፎ ባለመስጠት በታሪክ ፊት ሁልጊዜም አንጸባራቂ ድል ጽፏል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ አይበገሬነት በቃል ብቻ የሚገለጽ ሳይሆን በደም እና በዐጥንት የተረጋገጠ እውነት ነው። ከወረራዎች፣ ከጂኦ-ፖለቲካዊ ጫናዎች እና ከውስጣዊ የትግል ምዕራፎች በሻገር፣ እንደ ዓድዋ ባሉ ታላላቅ ታሪካዊ አጋጣሚዎች ኢትዮጵያውያን ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን በመተው ለሀገር አንድነትና ሉዓላዊነት በአንድነት ቆመዋል። ይህ ቁርጠኝነት ኢትዮጵያን የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ምልክት አድርጓታል።

ዛሬ ላይ ዓለማችን የተወሳሰበ የፖለቲካ እና የቴክኖሎጂ ምኅዳር ውስጥ ትገኛለች። በመሆኑም ሀገራችን የምትጋፈጣቸው ፈተናዎች እንደ ቀደመው ዘመን በመሳሪያ በሚደረግ ግልጽ ውጊያ ብቻ የተገደበ አይደለም። ይልቁንም የሕዝብን ሥነ-ልቦና ለማዳከም እና እርስ በርስ ለማጋጨት የሚነዙ ሐሰተኛ መረጃዎች፤ የሀገርን ሰላም ለማናጋት የሚደረጉ ድብቅ ስልቶች፤ በኢኮኖሚና በፖለቲካው የተደቀኑ ተጽዕኖዎች አዲሶቹ የትግል አውደ-ግንባሮች ሆነዋል።

እነዚህ አዳዲስ ዘመናዊ ፈተናዎች የሚጠይቁት ጥበብ፣ ትዕግሥት እና ጥልቅ አርቆ አሳቢነትን ነው። በዚህ የዘመናችን የፈተና ሂደት ውስጥ የሀገርን ጽናትና አይበገሬነት ለማስቀጠል የመንግሥት እና ሕዝቡ ጠንካራ አንድነት መኖሩ ወሳኝ ነው። በተለይም የወጣቱ ትውልድ አርቆ አሳቢነት ለነገዋ ኢትዮጵያ ሕልውና ወሳኝ መሠረት ነው።

ወጣቱ በመረጃ ጦርነት ውስጥ ሳይሸነፍ፣ የሐሰተኛ መረጃዎችን ዓላማ በመረዳት እና ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ እውነታዎች ላይ በማተኮር ሀገሩን መጠበቅ አለበት። ስሜታዊነትን በማስወገድ፣ በውይይትና በምክንያታዊነት የሀገርን ዘላቂ ጥቅም ማረጋገጥ የወጣቱ ኃላፊነት ነው። አባቶች ሀገርን በደም ጠብቀው እንዳስረከቡ ሁሉ፣ የአሁኑ ትውልድ ደግሞ በዕውቀት፣ በሥራ፣ በቴክኖሎጂ እና በጽናት የሀገርን ሉዓላዊነት የማስከበር ድርሻ አለበት።

ለዚህ ነው የመደመር መንግሥት ሁሉን አቀፍ በሆነ መንገድ ሉዓላዊነትን በማስጠበቅ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት እየተጋ የሚገኘው። በመደመር እይታ ሉዓላዊነት ማለት የሀገርን ወሰንና ግዛት በመከላከያ ሰራዊት መጠበቅ ብቻ ሳይሆን፣ የኢኮኖሚ፣ የምግብ፣ የዲፕሎማሲ፣ የመረጃ ፣የቴክኖሎጂ እና የስነ-ልቦና ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ነው። ከውጭ የሚገባውን ስንዴ በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት እና ወደ ውጭ መላክ በመጀመር የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ በግብርናው ዘርፍ በሰብል፣ በእንስሳትና በጓሮ አትክልት ምርቶች ራስን የመቻል ሥራዎች እንዲሁም ምርታማነትን ማሳደግ፣ የፋይናንስ ዘርፉን ማዘመን እና የውጭ ኢንቨስትመንትን የሚስቡ አሰራሮችን መዘርጋትም የመደመር መንግሥት ምሉዕ ሉዓላዊነት አንጓዎች ናቸው።

በተጨማሪም በዓለም አቀፍ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ምኅዳር ውስጥ የኢትዮጵያን ድምፅ ማጎልበት እና የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲን ማጠናከርም የኢትዮጵያን ጽናት እና አይበገሬነት ማስቀጠያ መንገዶች ናቸው። በሰላማዊ መንገድ እና በጋራ ተጠቃሚነት መርህን በመከተል የሀገርን የረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ እና የደህንነት ሉዓላዊነት የሚያረጋግጥ የባህር በር ለማግኘት የሚደረጉ ጥረቶች ይጠቀሳሉ።

በሌላ በኩል ምሉዕ ሉዓላዊነት ማረጋገጫ መንገዱ በሳይበር ዘርፍም የግድ መታገዝ ባለበት ዘመን ላይ እንገኛለን። የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር እና የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትን በማጠናከር ሀገሪቱን ከመረጃና ከሳይበር ጥቃቶች የመጠበቅ፣ እንዲሁም አዳዲስ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን የማልማት ሥራ ቁልፍ ጉዳዮች ናቸው።

ከሁሉም በላይ የመከላከያ ሰራዊቱን እና የደህንነት ተቋማትን በዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች፣ በድሮን ቴክኖሎጂዎች፣ በሳይበር ደህንነት እና በሙያዊ ብቃት ማደራጀት ጊዜው የሚጠይቀው ነው። የመደመር መንግሥት ነባር የሰራዊቱን ክፍሎች ዓለም በደረሰበት ደረጃ ከማዘመን ሥራው ጎን ለጎን ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስጠብቅ የባህር ኃይል ግንባታ ሥራዎችን በትኩረት እያከናወነ ይገኛል።

በጥቅሉ ኢትዮጵያ የጽናትና የአይበገሬነት ምልክት ሆና የዘለቀችው በአጋጣሚ ሳይሆን፣ በሕዝቧ አስተዋይነት፣ በቆራጥነቱ እና ለሉዓላዊነቱ ባለው ጥልቅ ፍቅር ነው። የዛሬው ዘመን ፈተናዎች ቢወሳሰቡም፣ የመንግሥትና ሕዝብ የተቀናጀ ጥረት እንዲሁም የወጣቱ አስተዋይነትና አርቆ አሳቢነት ሲታከልበት፣ ኢትዮጵያ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ፈተናዎችን አሸንፋ የጽናትና የነፃነት ምልክት ሆና ትቀጥላለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም