ቀጥታ፡

በሐረሪ ክልል የበጋ መስኖ ልማቱን ውጤታማ በማድረግ ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ

ሐረር ፣ጥቅምት 11/2019 (ኢዜአ) ፡-በሐረሪ ክልል የበጋ መስኖ ልማቱን ውጤታማ በማድረግ ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ።

በክልሉ በዘንድሮ በጋ የመስኖ ልማት ሥራ ለግብርና ባለሙያዎች ሥልጠና በመሰጠት ላይ ነው።


 

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የግብርና ልማት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሮዛ ኡመር በወቅቱ እንደተናገሩት፤ በክልሉ የውሃ አማራጮችን በመጠቀም ከ4 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ለማልማት ወደ ሥራ ተገብቷል።

በክልሉ የመስኖ ልማቱን ለማሳካት የምርጥ ዘርና የምርት ማሳደጊያ ግብዓት በወቅቱ ለአርሶ አደሩ መቅረቡንና ለግብርና ባለሙያዎች ሥልጠና እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

የበጋ መስኖ ልማቱን ውጤታማ በማድረግ ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ፣ ገበያን የማረጋጋት እና አርሶ አደሩን ከተረጂነት ማውጣት ዓላማ ማድረጉንም አስረድተዋል።

ለተግባራዊነቱም የግብዓት አቅርቦት፣ የክህሎት ሥልጠና እና የባለሙያ የቴክኒክ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

የመስኖ ልማቱን ውጤታማ በማድረግ በክልሉ በዝናብ እጥረት የተከሰተውን የምርት መቀነስ ለማካካስ እንደሚሠራም ጠቁመዋል።

በክልሉ በዘንድሮ የበጋ መስኖ ልማት የሽንኩርት፣ የቲማቲም፣ የጥቅል ጎመን፣ የቃሪያ፣ ካሮትና ሌሎች የአትክልትና የሰብል ዓይነቶች በስፋት የሚለሙ መሆናቸውን በቢሮው የግብርና ኤክስቴንሽን ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ መሐመድ ረድዋን ተናግረዋል።


 

በመስኖ ከሚለማው መሬትም ከ1 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን ጠቁመዋል፡፡

ሥራውን ለማሳካትም በየደረጃው ለሚገኙ የግብርና ባለሙያዎችና የልማት ጣቢያ ሠራተኞች እንዲሁም ለአርሶ አደሩ ሥልጠና መሰጠት መጀመሩን አቶ መሐመድ አክለዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም