በክልሉ የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ የእንስሳት እርባታ ዘርፍን በማሳደግ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ እያደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ የእንስሳት እርባታ ዘርፍን በማሳደግ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ እያደረገ ነው
አሶሳ፤ ጥቅምት 11/2019 (ኢዜአ)፡-በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ የእንስሳት እርባታ ዘርፍን በማጠናከር የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያሳደገ መምጣቱ ተገለጸ።
የክልሉ ግብርና ቢሮ እንስሳት እና ዓሣ ሀብት ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ብርሃኑ ኢትቻ (ዶ/ር) በአቡራሞ ወረዳ የተለያዩ ቀበሌዎች በዘርፉ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
በዚህ ወቅት ምክትል ቢሮ ሃላፊው ብርሃኑ ኢትቻ (ዶ/ር) አርሶ አደሩ በእንስሳት እርባታ ዘርፍ በመሰማራት ተጠቃሚ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል።
በርካታ አርሶ አደሮች በእንስሳት እርባታ ሥራ ተሰማርተው የኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸው፣ የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ ተግባራዊ መደረጉን ዘርፉን በማነቃቃት የአርሶ አደሩ ተጠቃሚነት እንዲያድግ አግዟል ብለዋል።
ለእዚህም በአቡራሞ ወረዳ አርሶ አደሮች ከግለሰብ ጀምሮ በማህበር ተደራጅተው በዶሮ እርባታና በእንስሳት ማድለብ ውጤታማ ሥራ እያከናወኑ እንደሆነ መመልከታቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች አርሶ አደሩ ከመደበኛ የእርሻ ሥራው ጎን ለጎን በእንስሳት እርባታ ዘርፍ በመሰማራት ተጠቃሚ እንዲሆን የተዳቀሉ የእንስሳት ዝርያዎች እየተሰራጩ መሆናቸውንም አመልክተዋል።
የአቡራሞ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አታላይ ደረጃ በበኩላቸው፤ በወረዳው አካታች እና አሳታፊ የግብርና ሥራዎች በመከናወናቸው ህብረተሰቡ በሁሉም ዘርፍ ተጠቃሚ እየሆነ መጥቷል።
የወረዳው አርሶ አደሮች በእንስሳት እርባታ ከሚያገኙት ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ባለፈ የተመጣጠነ ምግብ በማግኘት ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን እየተከተሉ ይገኛሉ ብለዋል።
የእንስሳት እርባታን ከመደበኛ የግብርና ሥራ ጋር በማቀናጀት አርሶ አደሩ ከሁሉቱም ዘርፍ ተጠቃሚ እየሆነ መምጣቱን ገልጸው፣ የሌማት ትሩፋት መርሀግብር ይህን ተጠቃሚነቱን አሳድጎታል ብለዋል።
በአቡራሞ ወረዳ የአምባ 14 ቀበሌ ነዋሪ አቶ ተፈራ ሞላ በዶሮ እርባታ የጀመሩትን ሥራ በማጠናከር ቤተሰባቸውን ከማስተዳደር ባለፈ ፍየሎችን የማርባት ሥራ መጀመራቸውን ተናግረዋል።
የእንስሳት እርባታ ሥራ አዋጭ መሆኑን ጠቁመው፣ ለእንስሳቱ የሚደረግላቸው የሕክምና፣ የመኖ እና ሙያዊ ድጋፍ ለውጤት እንዳበቃቸው ገልጸዋል።
በአቡራሞ ወረዳ "ማሻአላህ የዶሮ እርባታ ማህበር" ሊቀመንበር በድሪያ ሙስጠፋ በበኩላቸው፤ የአንድ ቀን ጫጩትን ተረክበው በማሳደግ ገቢ እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል።