በአማራ ክልል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ብልሹ አሰራርን እያስቀረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ብልሹ አሰራርን እያስቀረ ነው
ኮምቦልቻ፣ ጥቅምት 11/2019(ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የተገልጋይ እርካታን ከማሳደግ ባለፈ ብልሹ አሰራርን እያስቀረ መሆኑን የክልሉ ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።
ቢሮው በበጀት ዓመቱ ሩብ ዓመት በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም አፈጻጸም ላይ የሚመክር መድረክ በኮምቦልቻ ከተማ አካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የቢሮው ሃላፊ ወይዘሮ ባንቺአምላክ ገብረማሪያም እንደገለጹት፣ የተሻለ የተቋማት አደረጃጀትና የአሰራር ሥርዓት በመዘርጋት ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ተችሏል።
ለዚህም በአዲስ መልክ እየተተገበረ የሚገኘው የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርምን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል መመሪያና ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ መገባቱን አውስተዋል።
በክልሉ በስድስት ማዕከላት የተጀመረው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትም ፈጣን፣ ቀልጣፋና ፍትሃዊ አገልግሎት በመስጠት የተገልጋይ እርካታን ለማሳደግና ብልሹ አሰራርን ለማስቀረት ማስቻሉን ገልጸዋል።
ለእዚህም በተካሄደ ጥናት 99 ነጥብ 6 በመቶ የተገልጋይ እርካታን መፍጠር እንደተቻለ የጠቆሙት ሃላፊዋ፣ ውጤቱም በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የገቡ ተቋማት የአገልጋይነት መንፈስ በመላበሳቸው የመጣ ነው ብለዋል።
በተያዘው በጀት ዓመትም ይህን ወጤት ለማስቀጠል ተጨማሪ 149 መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ማዕከላትን ግንባታ ለማስጀመርና አራት ማዕከላትን ደግሞ ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
የደሴ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ሽመልስ ጌታቸው በበኩላቸው እንዳሉት፣ በከተማው አገልግሎት አሰጣጡን ዲጂታላይዝ በማድረግ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት ተችሏል።
በተለይ በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በርካታ አገልግሎቶችን አንድ ሥፍራ ላይ መስጠት መቻሉ የተገልጋይን እንግልት፣ ጊዜና ወጪን ከመቆጠብ ባለፈ ብልሹ አሰራርን አስቀርቷል ብለዋል።
የተገኘውን ውጤት ለማስቀጠል በሁለት ክፍለ ከተሞች ላይ ተጨማሪ መሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ለማስጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርሙን በሙሉ አቅም ወደ ትግበራ በማስገባት የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት እየተሰራ ነው ያሉት ደግሞ የደቡብ ወሎ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አሊ ይማም ናቸው።
አስተዳዳሪው እንዳሉት በዞኑ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት በዘጠኝ ከተማ አስተዳደሮች እና በ20 ወረዳዎች መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ሥራ ለማስጀመር ዝግጅት እየተደረገ ነው።
የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ብዙነሽ ሰይድ፣ በከተማ አስተዳደሩ የሲቪል ሰርቪስ አሰራርን በማዘመን የተሻለ አገልግሎት መስጠት መቻሉን አንስተዋል።
በመድረኩ ላይ የክልል፣ የዞንና የከተማ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።