ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞቿን ለማስጠበቅ የተከተለችው አዲስ የለውጥ እሳቤ ተጨባጭ ውጤት እያመጣ ነው-አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞቿን ለማስጠበቅ የተከተለችው አዲስ የለውጥ እሳቤ ተጨባጭ ውጤት እያመጣ ነው-አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ጥቅምት 11/2019 (ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞቿን ለማስጠበቅ የተከተለችው አዲስ የለውጥ እሳቤ ተጨባጭ ውጤት እያመጣ መሆኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር) ገለጹ።
አረጋዊ (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ኢትዮጵያ የቀይ ባህር ወደቦችንና የመርከብ መስመሮችን ለንግድ፣ለሀገር መከላከያ እና ለባህር ኃይል ግንባታ በመጠቀም ለዘመናት የዘለቀ የባህር ትስስር የነበራት ሀገር መሆኗን ገልጸዋል።
ዘይላ፣ምፅዋ እና አሰብ ታሪካዊ የኢትዮጵያ የባህር በሮች እንደነበሩ የጠቆሙት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ሀገሪቷ ወደ ባህር የምታደርገውን ቀጥታ የመውጫ መንገድ ማጣቷ በባህር ጉዳዮች ላይ ያላትን ህጋዊ መብትና ታሪካዊ ቁርኝት አያጠፋውም ብለዋል።
አክለውም ኢትዮጵያ በህጋዊና ዲፕሎማሲያዊ መንገድ የባህር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ መቀጠል አለባት ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ ጥያቄው ሕጋዊም ታሪካዊም መሰረት ያለው መሆኑን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የማስገንዘብ ሥራዎች ሊጠናከሩ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ አዲስና ውጤታማ መንገድ መከተል መጀመሯን ጠቅሰው፤ ይህም ተጨባጭ ውጤቶች እያመጣ መሆኑን አብራርተዋል።
የኢትዮጵያን የባህር በር ጥቅም ለማስጠበቅ በሚደረገው ጥረት ላይ የሕዝብ ድጋፍ እየጎለበተ መምጣቱን ያመለከቱት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ያለው ትስስርና መግባባት ሀገሪቷ ያቀደችውን ግብ ለማሳካት አቅም እየሆናት ነው ብለዋል።
የባህር በር ጉዳይ የህዝብ የዘመናት ቁጭት መሆኑን ጠቅሰው፤ መብታችንን የማናስከብርበት ምንም ዓይነት ምክንያት አይኖርም ሲሉም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ጥንታዊ መንግሥታዊ ተቋማትና የአስተዳደር ልምድ ለቀይ ባህር ቀጣና እና ከዚያ በላይ ለሆኑ አካባቢዎች ደጋፊና ዘላቂ ሰላም ማምጣት እንደሚችሉ አስረድተዋል።
የባህር ኃይል አቅምን መገንባት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ብቻ ሳይሆን ለሰፊው ቀጣናዊ የባህር ደህንነትም አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ገልጸዋል።
እንደ አረጋዊ (ዶ/ር) ገለጻ፤ ይህ አቅም ተጠናክሮ ሥራ ላይ ሲውል ለቀይ ባህር ቀጣና ብቻ ሳይሆን ለመላው የአፍሪካ አህጉር የሰላምና ደህንነት መረጋጋት መሠረት ሆኖ ሊያገለግል ይችላል።
ኢትዮጵያውያን በሀገር በቀል እውቀትና በጋራ ርብርብ ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን የመገንባት አቅም እንዳላቸው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን እውን ማድረጋቸው ጉልህ ማሳያ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ተመሳሳይ ቁርጠኝነትና ትብብር ሀገሪቱ በባህር በር ባለቤትነት ዙሪያ ትልሟን ለማሳካትና ለቀጣናው ሰላምና ደህንነት የምታደርገውን አስተዋጽኦ ለማጠናከር እንደሚያስችል አመልክተዋል።