ጥበብ የሕብር ኢትዮጵያ ማስተሳሰሪያ ገመድ፤ የዜጎቿ የወል እውነት መገንቢያ መሰረት!! - ኢዜአ አማርኛ
ጥበብ የሕብር ኢትዮጵያ ማስተሳሰሪያ ገመድ፤ የዜጎቿ የወል እውነት መገንቢያ መሰረት!!
በታዬ ለማ (ኢዜአ)፡- ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ሕዝብ፤ ታላቅ ርዕይ
ጥበብ የሰውን ልጅ ውስጣዊ ስሜት በመግለጽና የማኅበራዊ ትስስርን በማጠናከር የሀገርን ታሪክ፣ ባህል፣ ማንነትና ራዕይ ለትውልድ የሚያስተላልፍ የጋራ መግባቢያ ቋንቋ ነው። ሥነ-ጽሑፍ፣ ሙዚቃ፣ ቲያትር፣ ፊልምና ሌሎች የጥበብ ሥራዎች የሕዝቦችን የጋራ ታሪክና ተሞክሮ በማንጸባረቅ መግባባትና የጋራ ራዕይን በመቅረጽ የማይተካ ሚና አላቸው።
በሕብር ጌጦች ለአሸበረቀችው ኢትዮጵያ እነዚህ የጥበብ ሥራዎች ልዩ ትርጉም የሚሰጣቸው ናቸው። የኢትዮጵያውያን ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ዜማ፣ ውዝዋዜና ባህላዊ እሴቶችም ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚያንጹ የሀገር ሀብቶች ናቸው። በጥበብ አማካኝነት መተረካቸው ደግሞ የዜጎችን እርስ በርስ ትውውቅና ተሞክሮ በማጋራት የጋራ ሀገራዊ ማንነትን እያጠናከሩ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ጥበብ ከረጅም ታሪክ፣ ባህላዊ ብዝሃነት፣ ሃይማኖታዊ እሴቶችና የሉዓላዊነት ትግል ጋር ጥልቅ ትስስር አለው። በዓድዋ ድልና በሌሎች ሀገራዊ ፈተናዎች ወቅት ቀረርቶ፣ ፉከራና የሀገር ፍቅር ዜማዎች የሕዝቡን ወኔ በማነቃቃት የጀግንነትና የመሥዋዕትነት ታሪኮች እንዲተላለፉ አድርገዋል።
ከጥንታዊ የብራና ጽሑፎች፣ ከሃይማኖታዊ ሥዕሎችና ከፍልስፍና ሥራዎች ጀምሮ እስከ ዘመናዊ ሥነ-ጽሑፍ፣ ሙዚቃ፣ ቲያትርና ሲኒማ ድረስ የሚዘልቀው የኢትዮጵያ የፈጠራ ታሪክ የሥልጣኔ ዐሻራዎችን ይዟል። የባህላዊ ዘፈኖች፣ ምሳሌያዊ አነጋገሮችና ባህላዊ ክዋኔዎች ደግሞ ማኅበራዊ እሴቶችን በማጋመድ ለአብሮነትና የጋራ ሰላም ግንባታ ጉልህ ሚና ተወጥተዋል፤ እየተወጡም ነው።
በዚህ መሠረት ጥበብ የተለያዩ ታሪኮችንና በልዩነቶች መካከል የጋራ እሴቶችን የሚያጎላ፣ የተለያዩ ድምፆች እኩል ቦታ የሚያገኙበትን የመግባቢያ መድረክ የሚፈጥር ኃይል ነው። ይህም የኢትዮጵያውያንን የጋራ ትርክት በማጠናከር ለሰላም፣ ለማኅበራዊ ትስስርና ለሀገራዊ መግባባት የሚኖረውን ሚና ያሳያል።
ጥበብ የሀገርን ገጽታ በመገንባት፣ ባህልን በማስተዋወቅና የዜጎችን ሀገራዊ ኩራት በማጠናከር የሚኖረውን ሚና ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችም ያሳያሉ። ለአብነትም ሆሊውድ የአሜሪካን፤ ቦሊውድ የሕንድን ባህል፣ ታሪክና ማኅበራዊ እሴቶች በፊልም አማካኝነት በዓለም ዙሪያ በማስተዋወቅ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። ይህ ተሞክሮ ጥበብ የባህል መገለጫ ብቻ ሳይሆን የሀገር ገጽታን ለመገንባትና የባህል ዲፕሎማሲን ለማጠናከር የሚያገለግል መሣሪያ መሆኑን ያሳያል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሀገሪቱ የጥበብ ባለሙያዎች ጋር ባደረጉት ውይይት፤ ጥበብ ለሀገር ግንባታ፣ ለማኅበራዊ አንድነትና ዕድገት ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል። የጥበብ ሥራም ባህላዊ ቅርሶችን የመጠበቅ፣ የማኅበረሰቦችን ድምፅ በማሰማትና ማኅበራዊ ትስስርን በማጠናከር ጉልህ ድርሻ እንዳለውም ገልጸዋል። በትምህርት ዘርፍም ፈጠራንና ሂሳዊ አስተሳሰብን በማሳደግ በኢኮኖሚው ዘርፍ ለፈጠራ፣ ለቱሪዝምና ለሥራ ዕድል ፈጠራ ያለው አስተዋፅኦ የሚናቅ አይደለም። ይህም ጥበብ በሀገር ግንባታ፣ በሥልጣኔና በዘላቂ ዕድገት ጉልህ ድርሻ ያለው መሆኑን ያመላክታል።
የኢትዮጵያ ጥበብ ሰፊ ታሪካዊና ባህላዊ ሀብት ቢኖረውም ከአቅሙ ጋር የሚመጣጠን ዘላቂ ዕድገት እንዲያሳይ ተቋማዊና መሠረተ ልማታዊ ድጋፎች ተነፍገውት ቆይተዋል። በዚህም የመደመር መንግሥት የሥራ ቦታዎች፣ የቲያትር ቤቶች፣ የሲኒማ አዳራሾች፣ የሙዚቃ ስቱዲዮዎችና የጥበብ ማዕከላትን በማስፋፋት ጥበብና ጥበበኛ የሚገናኙበትን አስቻይ መድረክ ፈጥሯል።
በዚህ ረገድ በመደመር ፍልስፍና ሥር ጥበብና ባህልን ከሀገር ግንባታ፣ ከብሔራዊ መግባባትና ከኢኮኖሚ ዕድገት ጋር የማገናኘት አቅጣጫ ተቀምጧል። ከአዲስ አበባ እስከ ክልሎች የተከናወኑ የከተማ ልማትና የመሠረተ ልማት ሥራዎች፣ እንደ አብርሆት ቤተ-መጻሕፍት ያሉ የዕውቀት ማዕከላት፣ የባህላዊና ታሪካዊ ቦታዎች ዕድሳት፣ የኮሪደር ልማትና የገበታ ፕሮጀክቶች ግንባታ ለጥበብ፣ ለባህል፣ ለቱሪዝምና ለፈጠራ ሥራዎች አዳዲስ የዕድል መስኮቶችን ከፍተዋል።
የአዲስ አበባ ዘመናዊው የሕፃናትና ወጣቶች ቴአትርና ሲኒማ ኮምፕሌክስ፣ ነባር ቴአትር ቤቶች ዕድሳትና የአዳዲስ የጥበብ መድረኮችም የመደመር መንግሥት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት ያመላክታል። በተመሳሳይ የሲኒማ ቤቶች፣ አምፊቲያትሮችና ሌሎች የጥበብ መድረኮች መስፋፋት የጥበብ ሰዎች ሥራቸውን ለሕዝብ በማቅረብ የኢኮኖሚ አቅማቸውን በማጎልበት ተጨማሪ ሥራዎች የሚከወኑበትን ወሳኝ ዕድል ፈጥሯል።በትምህርት ዘርፍም ጥበብን ከሥርዓተ ትምህርት ጋር ማቀናጀት፣ በዩኒቨርሲቲዎች የሙያ ሥልጠናንና ምርምርን ማሳደግ ለቀጣዩ ትውልድ የፈጠራ አቅም መሠረት እየጣለ ይገኛል።
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰጥ የጥበብ ትምህርትና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሦስተኛ ዲግሪ መርሃ ግብር መጀመር ዘርፉን በሙያዊ ዕውቀትና በምርምር ለማጠናከር የተሰጠውን ትኩረት ያመለክታሉ። የጥበብ ውጤቶች ማኅበራዊ ግንኙነትን ከማጠናከር ባለፈ የኢኮኖሚ ዕድገት ምንጭ ናቸው። ሙዚቃ፣ ፊልም፣ ሥነ-ጽሑፍ፣ የዕደ ጥበብ፣ የባህል ፌስቲቫሎችና የፈጠራ ሥራዎች የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ፣ ቱሪዝምን ያበረታታሉ፣ ለትናንሽ ንግዶች ገበያን ይከፍታሉ።
የኢትዮጵያ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ልማት መስፋፋትም የኢትዮጵያን የጥበብ ውጤቶች ለዓለም አቀፍ ተመልካቾች ለማድረስ አዳዲስ ዕድሎችን ፈጥሯል። ይህን አቅም በተግባር በማሳደግ የጥበብ ሥራዎችን ከመፍጠር ባሻገር ለማምረት፣ ለማሰራጨት፣ ለማስተዋወቅና ለገበያ ለማቅረብ የሚያስችል የፈጠራ ኢንዱስትሪ እየተገነባ ነው። መንግሥት የፈጠረውን አስቻይ የጥበብ ኢንዱስትሪ ልማት አርቲስቶች፣ ባለሀብቶች፣ የትምህርት ተቋማትና መገናኛ ብዙኅን ዕድሉን መጠቀም ይጠበቅባቸዋል።
የኢትዮጵያ የጋራ ትርክት ግንባታ የሕዝቦችን ታሪክና ተሞክሮ በሕብረ ብሔራዊ ጌጥና ማንነት በመግለጥ በጋራ የሚያገናኙ እሴቶችን ማጠናከር ነው። ጥበብ በዚህ ረገድ ልዩ አቅም አለው። የጋራ ሀገራዊ መግባባትን ለመገንባትም በዘፈን፣ በተረት፣ በፊልምና በቴአትር አማካኝነት በስሜትና በማስተዋል እንዲመለከቱ ያስችላል።
የተለያዩ ማኅበረሰቦች የሚያቀርቧቸው የጥበብ ሥራዎች የጋራ ታሪክን በመገንባት፣ የጋራ ዕይታን በመቅረጽና ማኅበራዊ መስተጋብርን በማጠናከር ከፍተኛ ጠቀሜታ አላቸው። ይህ ደግሞ ለሀገራዊ መግባባት ከሚያስፈልጉት መሠረታዊ አምዶች አንዱ ነው።
የመደመር መንግሥት የፈጠረውን የጥበብ ልማት ሙያተኞች ከመድረክ ዝግጅት ባሻገር በፈጠራ ነፃነት፣ በሐሳብ ብዝሃነትና የሕዝብን ሀብት በማንጸባረቅ መጠቀም ይጠበቅባቸዋል።ይህ ሲሆንም የጥበብ ሥራዎች ለሕዝቡ የጋራ ውይይት መድረክ ሲሆኑ፣ ለሀገራዊ መግባባትና ለዘላቂ ሰላም የሚኖራቸው አስተዋፅኦ ይጠናከራል።
ኢትዮጵያ የበለፀገ የታሪክና የቱባ ባህል ሀብት ያላት ሀገር ናት። ይህን ሀብት ለትውልድ ማስተላለፍ፣ የተለያዩ ሕዝቦችን ታሪክና እሴቶች በእኩል ሁኔታ ማክበርና በጥበብ አማካኝነት የጋራ ራዕይን ማጠናከር የቀጣዩ ትውልድ የጋራ ኃላፊነት ነው።
የመደመር ፍልስፍና በጥበብና ባህል ዘርፍ ያለው ዋና ትርጉም የሚገለጸው የተለያዩ አቅሞችን ማቀናጀት፣ ልዩነቶችን እንደ ሀብት መመልከትና የጋራ ጥቅምን በትብብር ማሳደግ ሲቻል ነው። የጥበብ ባለሙያዎች የሕዝቡን ድምፅ በሥራዎቻቸው ሲያንጸባርቁ፣ መንግሥት የፈጠረውን ምቹ ምኅዳር፣ የግል ዘርፉ በኢንዱስትሪው ላይ ሲሳተፍና ሕዝቡ ለጥበብ ሥራዎች ተደራሽ ሲሆን የጥበብ ሀብት ወደ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ኃይል ይለወጣል።
ጥበብ የሀገርን ታሪክ የሚያስታውስ፣ የዛሬውን ማኅበረሰብ የሚያነጋግርና የነገውን ትውልድ የሚያነሳሳ የጋራ ቋንቋ ነው። ስለዚህ የኢትዮጵያን ጥበብ ማሳደግ የሀገሪቱን ባህላዊ ሀብት መጠበቅ፣ የፈጠራ ኢኮኖሚን ማጠናከር፣ የሕዝቦችን ድምፅ ማሰማትና የጋራ ሀገራዊ ትርክትን ማጎልበት ነው። ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ሕዝብ፤ ታላቅ ራዕይ የሰነቀችው ኢትዮጵያም በሕብር ያሸበረቁ ሕዝቦቿን ታሪክና ባህል እኩል በማክበር ጥበብ ለሁሉም የሚደርስ የመግባቢያ ቋንቋና የጋራ ዕድገትን የሚቀርጽ የአደባባይ መድረክ ሆኖ ያገለግላል።