ቀጥታ፡

ጤናማ ትውልድን ለመገንባት የአፍላ ወጣቶች የጤና ተሳትፎን ማጎልበት ይገባል

ሰመራ ፤ጥቅምት 11/2019 (ኢዜአ)፡- ጤናማ ትውልድን ለመገንባት የአፍላ ወጣቶች የጤና ተሳትፎንና ቅንጅታዊ አሰራርን ማጎልበት እንደሚገባ ተገለጸ።

የአፍላ ወጣቶችን ሁለንተናዊ የጤና ተሳትፎ በማጎልበት፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ያለመ 7ኛው የአፍላ ወጣቶች የጤና ምክር ቤት ፎረም በሰመራ ከተማ ተካሄዷል።


 

በፎረሙ ላይ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የወጣት ምክር ቤት ተወካዮች እና ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን፤ የአፍላ ወጣቶችን ጤና የመጠበቅና ተሳትፏቸውን የማሳደግ ጉዳይ ለአገር ግንባታ ባለው ፋይዳ ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል።

በፎረሙ ላይ በጤና ሚኒስቴር የእናቶች፣ ሕፃናትና አፍላ ወጣቶች መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰኚ ዱፌራ፤ የአፍላ ወጣቶች ጤና መጠበቅ ብቁና አምራች ዜጋን ለመገንባት የሚደረገው ጥረት ወሳኝ አካልና መሠረት መሆኑን ነው ብለዋል።

ሚኒስቴሩ ለወጣቶች የተለያዩ የጤና ችግሮች እንደ ሥነ-ተዋልዶ ጤና፣ የአእምሮ ጤና እና ሱስ የሚያጋልጡ መንስኤዎችን በሳይንሳዊ መንገድ ለመለየትና መፍትሔዎችን ለማስቀመጥ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

ስኬታማነቱም በየደረጃው ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ ወጣቶች ራሳቸው በመፍትሔ አፍላቂነትና በአስፈጻሚነት እንዲሳተፉ በጋራ እየተሠራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።


 

በአፋር ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የወጣቶች፣ ባህልና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አህመድ ኢብራሂም በበኩላቸው፤ የወጣቶችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ በላቀ ደረጃ ለማሳደግ ጤንነታቸው የሚጠበቅበትን ሥርዓትና ተደራሽነት ማጎልበት ቀዳሚ ተግባር ነው ብለዋል።

በክልሉ በአፍላ ወጣቶች የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ ተግዳሮቶችን በዘላቂነት ለመቅረፍ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የቅንጅት አሠራር ተጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቀዋል።

የአፋር ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ያሲን ሀቢብ፤ የአፍላ ወጣቶች የጤና አገልግሎቶችን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ ከአጋር አካላት ጋር ተቀናጅቶ መሥራት ለስኬቱ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።


 

ወጣቶች በማኅበረሰባዊ የጤና ንቅናቄዎች ላይ የሚያደርጉት ንቁ ተሳትፎ ለጤናው ዘርፍ ዕድገትና ለበሽታዎች መከላከል የጎላ ድርሻ እንዳለውም አክለዋል።

ፎረሙ አፍላ ወጣቶች የሚያጋጥሟቸውን የጤና ሥጋቶች በጋራ በመለየት፣ መፍትሔ የመስጠት ከፍተኛ አቅም እንዳለውም ጠቁመዋል።


 

የአፋር ክልል አፍላ ወጣቶች ጤና ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ወጣት መሐመድ ሁመድ በበኩሉ፤ ወጣቶች የአርብቶ አደሩን ማኅበረሰብ ጉልበትና እውቀት እያገለገሉ ናቸው ብለዋል።

ወጣቶች በበጎ ፈቃደኝነት የጤና አገልግሎት ዘርፍ በስፋት በመሰማራት ጤንነቱ የተጠበቀ፣ ንቁና አምራች ዜጋን በመፍጠር ረገድ ግንባር ቀደም ሚና እየተወጡ መሆኑን አስረድቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም