ቀጥታ፡

ከመከላከያ ሠራዊት ጎን በመሰለፍ ለሀገራዊ አንድነትና ለዘላቂ ሰላም የበኩላችንን እንወጣለን -የሀርቡ ከተማ ነዋሪዎች

ሀርቡ፤ ጥቅምት11/2019 (ኢዜአ)፡-ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን በመሰለፍ ለዘላቂ ሰላምና ሀገራዊ አንድነት መጠናከር የድርሻቸውን እንደሚወጡ በደቡብ ወሎ ዞን የሀርቡ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

በደቡብ ወሎ ዞን የሀርቡ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች የሀገር መከላከያ ሠራዊት የኢትዮጵያን ሰላምና ሉአላዊነት ለማስቀጠል እየከፈለ ያለውን መስዋዕትነት የሚደግፍ ሰላማዊ ሰልፍ ዛሬ አካሂደዋል።

የሰልፉ ተሳታፊ አቶ ሀሰን ኢብራሂም የሀገር መከላከያ ሠራዊት የአንድነት ማሳያ፣ የሰላምና ደህንነታችን ዋስትና እንዲሁም የሀገር ኩራትና ክብር መገለጫ መሆኑን አንስተዋል። 


 

ሠራዊቱ ለነፍሱ ሳይሳሳ በታላቅ ተጋድሎ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር በማስከበር ሉአላዊነቷን ከማረጋገጥ ባለፈ ለዘላቂ ሰላምና አንድነታችን ተግቶ እየሰራ ነው ብለዋል።

የሀርቡ ከተማ ነዋሪዎችም ከጎኑ በመሰለፍ  ዘላቂ ሰላምና አንድነትን ለማረጋገጥ የድርሻችንን ለመወጣት ዝግጁ መሆናችንን ለማሳየት ዛሬ ድጋፋችንን በሰላማዊ ሰልፍ አሳይተናል ብለዋል።

ሠራዊቱ የባዳ ተላላኪ የሆኑ ባንዳ እና ጽንፈኛ አካላትን ግልጽና ድብቅ ሴራ በማክሸፍ ዛሬም ጀግንነቱን በተግባር እያረጋገጠ በመሆኑ ኩራትና ደስታ ይሰማናል ብለዋል።

''እኔም ሠራዊቱ የቆመለትን ህዝባዊ አደራ በአሸናፊት እንዲወጣ ደጀን ከመሆን ባለፈ በማንኛውም ጊዜና ቦታ ከጎኑ ለመቆም ዘግጁ ነኝ" ብለዋል።

ሌላው የሰልፉ ተሳታፊ አቶ ይገዙ ጉታይ በበኩላቸው፣ የሀገር የመከላከያ ሠራዊት የሀገርን ክብርና ሉዓላዊነት ያስጠበቀ  የአንድነታችን አርማና ምልክት መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም ህዝቡ ከሠራዊቱ ጎን በመሰለፍ ደጀን ከመሆን ባለፈ ከጎኑ በመቆም አስፈላጊውን ዋጋ ለመክፈል ዝግጁና ቁርጠኛ ነን ብለዋል።

ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር ተሰልፈው ሀገር ለማፍረስ የሚታትሩ የውስጥ ተላላኪና ባንዳዎች እንቃወማለን፣ ሠራዊቱ ከሌሎች የጸጥታ አባላት ጋር በጥምር እየወሰደ ያለውን እርምጃ እንደግፋለን ብለዋል።

ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን በመሰለፍ ዘላቂ ሰላምና ሀገራዊ አንድነትን ከማስጠበቅ ባለፈ ለብሔራዊ ጥቅም መከበር የበኩላቸውን እንደሚወጡ የተናገሩት ደግሞ ወይዘሮ ዘሀራ ይመር ናቸው።

ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ያላቸው ክብርና ድጋፍ ሰላማዊ ሰልፍ በመውጣት መግለፃቸውን ተናግረዋል።

የድጋፍ ሰልፉ ተሳታፊዎች "ለድል የተወለደው መከላከያ ሠራዊታችን አለኝታችን ነው! ፣ በማይናወጠው የመከላከያ ሠራዊታችን የጀግንነት ተጋድሎ የሀገራችንን ክብር ከፍ እናደርጋለን! ፣ የኢትዮጵያን ጠላቶች እየደመሰስን ሰንደቅ ዓላማችንን ከፍ እናደርጋለን! የሚሉና መሰል መፈክሮችን አንግበዋል።


ሀርቡ ከተማን ጨምሮ በደቡብ ወሎ ዞን በተለያዩ አካባቢዎች ዛሬ በተካሄደው የመከላከያ ሠራዊት የድጋፍ ሰልፍ የሐይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ነዋሪዎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች ሌሎችም ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም