ቀጥታ፡

በከተማው የወጣቱን እውቀትና የሥራ ክህሎት በማሳደግ ለኢንዱስትሪዎች የሰለጠነ የሰው ኃይል የማቅረብ ተግባር እየተከናወነ ነው

ጎንደር፣ ጥቅምት 11/2019 (ኢዜአ)፡- በጎንደር ከተማ የወጣቱን እውቀትና የሥራ ክህሎት በማሳደግ ለኢንዱስትሪዎች የሰለጠነ የሰው ኃይል የማቅረብ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን የጎንደር ከተማ አስተዳደር የሥራና ክህሎት መምሪያ አስታወቀ።

በጎንደር ከተማ በሚገኙ ኢንዱስትሪዎች የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል የሥራ ላይ ልምምድና ሥልጠና ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ዛሬ ተካሄዷል።


 

የመምሪያው ኃላፊ አቶ አበበ ላቀው በዕለቱ እንደገለጹት፤ የወጣቱን እውቀትና ክህሎት በማሳደግ አምራች ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማቅረብ እየተሠራ ነው።

በዚህም በዓለም ባንክ ድጋፍ ባለፉት ሦስት ዓመታት በከተማዋ ከ4 ሺህ 400 በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ ዕድል በመፍጠር ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

በዚህ በጀት ዓመትም ለ2 ሺህ 376 ወጣቶች በኢንዱስትሪዎች ውስጥ የሥራ ላይ ልምምድ እንዲያገኙ በማድረግ፣ ከዚህ ውስጥ 1 ሺህ 901 ለሚሆኑት ቋሚ የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ይደረጋል ብለዋል።

ዛሬ በተጀመረው የሥራ ላይ ሥልጠና የሚሳተፉ ወጣቶችም በሚያገኙት እውቀት፣ ክህሎትና ልምድ መሰረት ከ700 በላይ ከሚሆኑ ቀጣሪ ድርጅቶች ጋር የማገናኘት ሥራ እንደሚሠራ አስረድተዋል ።

ለስድስት ወራት በሚቆየው ሥልጠና ላይም በሚሰማሩበት ዘርፍ በተግባር የተደገፈ እውቀት እንደሚያገኙ መምሪያው አስታውቋል።


 

በሥልጠናው ተሳታፊ የሆነው ወጣት ዑመር አህመድ መሐመድ በበኩሉ፤ በልብስ ስፌት በመሠልጠንና የሥራ ላይ ልምምድ በማድረግ በቀጣይ ሥራ ፈጣሪ ለመሆን እየሠለጠ መሆኑን አስረድቷል።

ሌላኛዋ በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የተሳተፈችው ሰላማዊት ለምከሙ በበኩሏ፤ ሥልጠናው በተግባር መሰጠቱ ለወደፊት ሙያዊ ብቃቷን በማዳበር የተሻለ ቦታ ላይ ለመድረስ እንደሚያስችላት አስረድታለች።


 

በሆቴል እና ቱሪዝም ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላት የገለጸችው ወጣቷ፤ የተጀመረው ሥልጠናም ፍላጎቷን እውን ለማድረግና ሙያውን በበለጠ ለማዳበር ትልቅ አጋጣሚ እንደሚፈጥርላትም አስረድታለች።

በሥልጠና ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይም የዘርፉ የሥራ ኃላፊዎች፣ ለሥልጠናው የተመለመሉ ወጣቶችና ቀጣሪ ድርጅቶች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም