በዞኑ የከርሰ ምድርና የገጸ ምድር ውሃን በመጠቀም ከዝናብ ጥገኝነት የተላቀቀ የአመራረት ባህልን ለማጎልበት ትኩረት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ የከርሰ ምድርና የገጸ ምድር ውሃን በመጠቀም ከዝናብ ጥገኝነት የተላቀቀ የአመራረት ባህልን ለማጎልበት ትኩረት ተደርጓል
ደብረ ማርቆስ፣ ጥቅምት 11/2019 (ኢዜአ)፡- በምስራቅ ጎጃም ዞን የከርሰ ምድርና የገጸ ምድር ውሃን በመጠቀም ከዝናብ ጥገኝነት የተላቀቀ የአመራረት ባህልን ለማጎልበት ትኩረት መደረጉን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።
መምሪያው የ2019 በጀት ዓመት የበጋ መስኖ ልማት የንቅናቄ መድረክ ዛሬ በደብረ ማርቆስ ከተማ አካሂዷል።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዋለ አባተ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ በዞኑ የከርሰ ምድርና የገጸ ምድር ውሃን በመጠቀም ከዝናብ ጥገኝነት የተላቀቀ የአመራረት ባህልን ለማጎልበት በትኩረት እየተሠራ ነው።
በዚህም የበጋ መስኖ ልማትን በማጠናከር በምግብ ራስን ከመቻል አልፎ ለኢንዱስትሪዎች ግብዓትና ለወጪ ንግድ የሚሆን ምርትን ለማምረት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
የመስኖ ምርታማነትን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት አስተዳደራቸው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
የዞኑ ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ጥላሁን ንጋቱ በበኩላቸው፤ በበጋው ከ131 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ በማልማት ከ13 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል።
ከዚህ ውስጥም ከ34 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነውን በበጋ መስኖ ስንዴ በማልማት ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል።
ከ475 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ በሚካሄደው የመስኖ ልማት በየአካባቢው ያሉ የውሃ አማራጮችን በስፋት ለመጠቀም እየተሠራ ነው ብለዋል።
የመስኖ ልማቱን ምርታማነት ለማሳደግም የኩታ-ገጠም አሠራር፣ የምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ግብዓትን በወቅቱ የማቅረብ ሥራ እየተካሄደ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ከተሳታፊዎች መካከል የደብረ ኤልያስ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌትነት ሰውአለም፤ የወረዳውን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በበጋ መስኖ ላይ በማተኮር እየተሠራ ነው ብለዋል።
አሁን ላይ የእርሻ ሥራ ተጀምሯል ያሉት አቶ ጌትነት፣ የደረሱ ሰብሎችን ፈጥኖ በማንሳት የመስኖ ሥራውን አጠናክሮ ለማስቀጠል እንደሚሠራም ተናግረዋል።
በንቅናቄ መድረኩ የዞንና የወረዳዎች የሥራ ኃላፊዎች፣ የዘርፉ ባለሙያዎች እና አጋር አካላት ተሳትፈዋል።