ቀጥታ፡

አፍሪካዊት የብልፅግና ተምሳሌት ኢትዮጵያ፤ ከጥገኝነት ወደ ብዝኅ-ዘርፍ ብሩህ የዕድገት አድማስ

በየፀዳወርቅ ታደለ (ኢዜአ)

ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ሕዝብ፤ ታላቅ ርዕይ

ኢትዮጵያ ለረጅም አስርት ዓመታት ስትከተለው የነበረውና በግብርና ብቻ የተንጠለጠለ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሀገሪቱ በሌሎች ቁልፍ ዘርፎች ልታመጣ የምትችለውን ሁለንተናዊ እመርታ አቆርቁዞት ቆይቷል። ዜጎችም በባህላዊ እርሻና በጥገኝነት አስተሳሰብ ውስጥ እንዲታጠሩ በማድረግ ለድህነትና ሁለንተናዊ ተጋላጭነት ምክንያት ሆኖ ሰንብቷል።

በኢትዮጵያ ሀገራዊ ለውጥ ማግስትም የመደመር መንግሥት የተለመው የብዝኅ ኢኮኖሚ ልማት ፍኖት የነጠላ-ዘርፍ ልማትን አስቀርቷል። ይህም የሁለንተናዊ ዕድገት ማማ ላይ ለማስቀመጥ የሚያስችሉ መዋቅራዊ፣ ደፋርና ስትራቴጂክ የፖሊሲ ማሻሻያዎች እንዲተገበሩ ዕድል ፈጥሯል።

የመደመር መንግሥት የብዝኅ ኢኮኖሚ የግብርና፣ ቱሪዝም፣ ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን እና አይሲቲ (ICT) ዘርፎችን አዲስ የልማት አድማሶች ማስፋት አስችሏል። የብዝኅ ኢኮኖሚ ዘርፍ የትኩረት መስኮችም ጸጋን ለይቶ በማልማት በአጭር ጊዜ ውስጥ አመርቂ የምርታማነት ዕድገትን መተለም ያስቻለ ትልቅ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል።

ይህ ሀገር በቀል የማክሮ-ኢኮኖሚ እና የልማት ስትራቴጂም የዜጎችን የፈጠራና የአምራችነት አድማስ በማስፋት የጥገኝነትና ተረጂነት አስተሳሰብን መስበር ያስቻለ አዲስ ባህል ገንብቷል። የቅርብ ዓመታት የኢትዮጵያ ዘርፈ-ብዙ ተከታታይ ስኬቶችም ለዘመናት በአስመጪነት ተንጠልጥሎ ቆየውን የኢኮኖሚ ሥርዓት ወደ ላኪነት ማሸጋገር አስችሏል። ይህ የዜና ትንታኔም ሀገሪቱ በቴክኖሎጂና በኢኮኖሚ ዘርፎች እያሳየች ያለችውን ድንቅ አዲሱን የማድረግ አቅም በዝርዝር ይዳስሳል።

ዘርፈ ብዙ  የልማት ትሩፋት፤ ኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ ትርፍ አምራች ሀገር

የመደመር መንግሥት ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን እንደ ቁልፍ መሣሪያ በመጠቀም ሀገሪቱን ከቀድሞው የተረጂነት አዘቅት አውጥቶ ወደ ራስን የመቻል አቅም አሸጋግሯታል። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነትና ቁርጠኛ አቋም በስንዴ ምርታማነት አብነት እያደረጋት ነው። ይህም ከውጭ የምታስገባውን አስቀርቶ ለውጭ ገበያ ኤክስፖርት ማድረግ ያስቻለ፣ በዓድዋ ድል ከተመዘገበው አኩሪ ታሪክ ጋር የሚመጣጠን ትልቅ ዐሻራ ሆኗል።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብርም በአካባቢ ጥበቃ፣ በደን ሽፋን ልማትና የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ አርዓያ የሆነ ሥራ ተከናውኗል። ኢትዮጵያም መርሃ ግብሩ ከተጀመረ አንስቶ ከ56 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን መተከል ችላለች።

በሩዝ ምርታማነትም በፎገራና በሌሎች አካባቢዎች የተከናወነው የሩዝ ልማት የውጭ ምንዛሬ ብክነትን በመታደግ በምግብ ራስን የመቻል ጉዞን አፋጥኗል። የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብርም በእንስሳት፣ ዶሮ፣ ዓሳ ሃብት እንዲሁም በከተሞች የጓሮ አትክልት ልማት አዲስ የንቅናቄ ማዕበል ተፈጥሯል። ይህም ዜጎች የተመጣጠነ የምግብና የሥነ-ምግብ ሥርዓትን በማሻሻል ጤናማ ዜጋን ማፍራት የሚያስችል እመርታዊ ውጤት ማስገኘቱን ቀጥሏል።


 

የኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት፤ ከሀገር ውስጥ የምርት አቅርቦት እስከ ዓለም ገበያ

የኢትዮጵያ የታምርት ንቅናቄ ዋና ዓላማ የሀገር ውስጥ ምርትን ማሳደግ፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ጥገኝነት በመቀነስና ኢትዮጵያዊ ምርቶችን በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ማድረግ ነው። ይህም ተኪ ምርትን በማስፋፋት፣ የምርት ጥራትን በማሻሻልና የማምረቻ ወጪን በመቀነስ የውጭ ምንዛሬ ወጪን ለመቆጠብና የወጪ ንግድ ገቢን እያሳደገ ይገኛል።

ሌላኛው የኢንዱስትሪ ልማት አስፈላጊነት የሥራ ዕድል ፈጠራ ነው። አዳዲስ ፋብሪካዎችና የማቀነባበሪያ ድርጅቶች ሲስፋፉ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ይፈጠራል። የሠራተኞች ክህሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግርም ይጠናከራል። በተለይም ከግብርናና ከእንስሳት ሀብት የሚገኙ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማቀነባበር አርሶ አደሩንና አርብቶ አደሩን ከኢንዱስትሪው ጋር ማስተሳሰር የገበያ ዕድልን ያሰፋል፣ ተጨማሪ እሴትን ይፈጥራል፣ የገቢ ምንጮችንም ያሳድጋል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄም በተኪ ምርት፣ በወጪ ንግድ፣ በሥራ ዕድል ፈጠራና በኢንዱስትሪ የንግድና ኢንቨስትመንት መስፋፋት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል። የኢትዮጵያ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮችም የአርሶና አርብቶ አደሩን ምርቶች በዘመናዊ የማቀነባበር ሥልት በማበልጸግ እሴት የታከለበት ምርት ለገበያ የሚቀርብበትን ዕድል ፈጥረዋል። እነዚህ ውጤቶች በተጨባጭ መረጃ ሲደገፉ፣ የኢትዮጵያን የምርት አቅም፣ የኢኮኖሚ ነፃነትና የዘላቂ ዕድገት አቅጣጫ በግልጽ እየበየኑ መምጣታቸውን ያሳያል።

የኢትዮጵያ የማዕድን ሀብት ልማት፤ ከምድር ውስጥ የተፈጥሮ ሀብት ወደ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት

የኢትዮጵያ የማዕድን ሀብት ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት፣ ለውጭ ምንዛሬ ገቢ ዕድገት፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለኢንዱስትሪ ልማት ወሳኝ አቅም ነው። የወርቅ፣ የታንታለም፣ የፖታሽና ሌሎች የከበሩ ማዕድናት ሀብቶችም የኢኮኖሚ ዕድገትን እየደገፉ ይገኛል።

የዘርፉን አቅም ወደ ተጨባጭ ውጤት ለመቀየር ማዕድናትን በጥሬ ዕቃነት ከመላክ በተጨማሪ በሀገር ውስጥ የማቀነባበርና እሴት የመጨመር አቅም እያደገ መጥቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በቅርቡ በቦሌ ለሚ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣና ተገንብቶ የተመረቀው ብሔራዊ የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካም በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የወርቅ ማጣሪያ ፋብሪካና ከአፍሪካ ግዙፍ የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ተቋማት አንዱ ነው። ፋብሪካውም ወርቅ ማጣራትና ተጨማሪ እሴት ለመፍጠር ቀጣናዊ ማዕከል የመሆን ዓላማን ሰንቋል።

ዓመታዊ አቅሙ የመጀመሪያው ምዕራፍ ሙሉ አቅሙን ሲይዝ በዓመት ከ600 ቶን በላይ ውድ ማዕድናትን የማጣራት አቅም አለው። በግምት 80 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ እንደሚያስገኝ ይጠበቃል። ይህም ኢትዮጵያ አጠቃላይ የማዕድን ሀብቷን እሴት በመጨመር ሁለንተናዊ ዕድገት መንገዷን በትክክለኛ መስመር እያለመች መሆኗን ያመላክታል።


 

የኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ ስኬት፤ ከታሪክ ውርስ ወደ አዲስ እመርታዊ ውልደት

የኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ የታሪክ፣ የባህል፣ የተፈጥሮና የቅርስ ሀብቶችን ወደ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የመቀየር ትልቅ አቅም አለው። የመደመር መንግሥትም አዳዲስ መሠረተ ልማቶችን በመገንባት ታሪካዊ ቅርሶችን በማደስ የኢኮኖሚ ዕድገትን የሚደግፍ ስኬት እያመጣ ነው።

የቱሪዝም ልማትም የውጭ ምንዛሬ ገቢን በማሳደግ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለሆቴሎችና የመጓጓዣ አገልግሎቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በማሳደግ ለኢኮኖሚ ዕድገት የማይተካ ሚና እየተወጣ ነው። ለአብነትም በ2018 ዓ.ም በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ የውጭ ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ከ5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አስገኝተዋል።

የቴክኖሎጂ ዘርፍ፤ ከዲጂታል ተጠቃሚነት ወደ አፍሪካ የኢኖቬሽን ማዕከልነት

የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የዲጂታል ሽግግርን የሚያሳልጥ ሁነኛ መሠረት ጥሏል። ወደ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ሽግግር በማድረግም የዲጂታል ክፍያ ሥርዓቶች መስፋፋት፣ የፋይዳ ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ትግበራ፣ መሶብ የአንድ ማዕከል፣ ተንቀሳቃሽና የተቀናጀ የሞባይል መተግበሪያ የመንግሥት አገልግሎቶች ሥርዓትም የአገልግሎት አሰጣጥን በማፋጠን መልካም አስተዳደርን እያስፈኑ ይገኛሉ።


 

የቴሌኮም አገልግሎት መሠረተ ልማት መስፋፋትም ወጣቶች የኮዲንግ፣ ዳታ ሳይንስ፣ ሰው ሠራሽ አስተውሎት እና ሶፍትዌር ልማት ዕውቀትና ክህሎታቸውን የሚያበለጽጉበትን ዕድል ፈጥሯል። ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 በፈጠረው መሠረት የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ዲጂታል ኢኮኖሚን ማሳደግ፣ የኢኖቬሽንና የስታርት-አፕ ምኅዳርን ማጠናከርና ኢትዮጵያን በአፍሪካ የዲጂታል ኢኮኖሚ ማዕከል ለማድረግ የሚያስችል አቅጣጫ ከፍቷል።

በአጠቃላይ የኢትዮጵያን የግብርና፣ የኢንዱስትሪ፣ የማዕድን፣ የቱሪዝምና የዲጂታል ዘርፎች ልማት ስንመለከት የተፈጥሮ ሀብትና የሰው ኃይል ሲሰናሰሉ የኢኮኖሚ አቅም ወደ ተጨባጭ ውጤት እየተቀየረ መሆኑን ያመላክታል። በግብርና የምርታማነት፣ በኢንዱስትሪ ተኪ ምርት፣ በማዕድንና ቱሪዝም ልማት፣ በዲጂታል ዘርፎች ለኢትዮጵያ ዕድገት ወሳኝ አቅጣጫዎች ተልመዋል።

“ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ሕዝብ፤ ታላቅ ርዕይ” የሰነቀችው ኢትዮጵያ የዕድገት ምኞቷን የሚበይኑ የልማት ትልሞቿን እያፋጠነች ነው። ይህ ራዕይም በተገኙ ውጤቶች፣ በተፈጠሩ የሥራ ዕድሎች፣ በሕዝብ የኑሮ መሻሻልና ዘላቂ ዕድገት እየተገለጠ ነው። ኢትዮጵያን አፍሪካዊት ፋና ወጊ የብልፅግና ተምሳሌት የማድረግ ህልም እውን የሚሆንበት ጊዜ ሩቅ አይደለም።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም