ቀጥታ፡

ጣና ፎረም የአፍሪካ ጉዳይ በአፍሪካውያን አንደበት የሚንጸባረቅበት የሀሳብ መድረክ ነው

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 11/2019 (ኢዜአ) ፦ጣና ፎረም የአፍሪካ ጉዳይ በአፍሪካውያን አንደበት የሚንጸባረቅበት የሀሳብ መድረክ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው ገለጹ።

የአፍሪካን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማዕከል በማድረግ በአሕጉሪቱ ሰላምና ደህንነት ላይ የሚመክረው የጣና ፎረም ለ15 ዓመታት በስኬት ተካሂዷል።

12ኛው የዘንድሮው የጣና ፎረም ''አፍሪካን ወደ ሰላም የሚወስዱ መንገዶች፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትና የቀጣናዊ ፖለቲካዊ ሽግግር” በሚል መሪ ሐሳብ የፊታችን አርብ በባሕር ዳር ከተማ ይጀምራል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው ለኢዜአ እንዳሉት፤ በዓለም ላይ ያሉ የሰላምና ደህንነት መድረኮች ለአካባቢያቸው ወይም ለፖለቲካ አጀንዳቸው ቅርብ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የሚመክሩ ናቸው።

የጣና ፎረም ለየት የሚያደርገው የአፍሪካ ጉዳዮች በአፍሪካውያን አንደበት የሚንጸባረቁበት መድረክ መሆኑ ነው ብለዋል።

ፎረሙ የሀገር መሪዎች ሀሳባቸውን በነፃነት የሚገልጹበትና በአህጉራዊ የሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ላይ ሀሳብ የሚቀያየሩበት መሆኑን ገልጸዋል።

በአፍሪካ የሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ላይ መፍትሔ አመላካች የሆኑ ሀሳቦችን የሚለዋወጡበት መድረክ ነው ብለዋል።

የጣና ፎረም የመድረክ አወቃቀር "የዛፍ ሥር ውይይት" ከሚባለው ከአፍሪካውያን ሀገር በቀል ልምድ የተቀዳ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ማህበረሰቡ ግጭቶችና አለመግባባቶችን የሚፈታባቸው የዛፍ ሥር ውይይቶች እንዳሉ ገልጸው፤ ጣና ፎረም "ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ" የሚል ማጠንጠኛ አለው ብለዋል።

የጣና ፎረም ለአፍሪካውያን ዘላቂ ሰላም የሚበጁ የአፍሪካውያን ሀሳቦች የሚገኙበት ነው ያሉት አምባሳደር ነቢያት፤ ሀሳቦቹ በአፍሪካ መደበኛ በሆኑ የሰላምና ጸጥታ ሰነዶች ውስጥ የሚገቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም