ዘመናዊ ግብርና የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ራስን የመቻል ጉዞን እውን ያደርጋል - ኢዜአ አማርኛ
ዘመናዊ ግብርና የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ራስን የመቻል ጉዞን እውን ያደርጋል
ሸገር፣ ጥቅምት 11/2019 (ኢዜአ) ፡-ዘመናዊ ግብርና የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ራስን የመቻል ጉዞን እውን ያደርጋል ሲሉ የሸገር ከተማ ምክትል ከንቲባና የገጠር ልማት ዘርፍ አስተባባሪ አቶ መሪድ ድምሩ ገለጹ።
በሸገር ከተማ ኮዬ ፈጬ ክፍለ ከተማ ገላን አራብሳ ወረዳ በኩታገጠም ምርጥ ዘር የስንዴ ልማት የመስክ ምልከታ ተካሄዷል።
የሸገር ከተማ ምክትል ከንቲባና የገጠር ልማት ዘርፍ አስተባባሪ አቶ መሪድ ድምሩ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ዘመናዊ ግብርና፡ የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ራስን የመቻል ጉዞን እውን ያደርጋል።
በተለይም የስንዴ ምርታማነት በአጭር ጊዜ ውስጥ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥና ከአቅርቦት ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ከፍተኛ ሚና አለው ብለዋል።
በሸገር ከተማም እነዚህን ግቦች ለማሳካት ያሉትን አቅሞች ወደ ስራ በመቀየር በርካታ ተግባራት በመከናወን ላይ ይገኛሉ ነው ያሉት።
በመርሐ ግብሩ በክረምት ዝናብ የለማ የኩታገጠም የስንዴ ልማት ኢንሼቲቭ የተጎበኘ ሲሆን፣ ይህም በግብርናው ዘርፍ የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን ለማስፋፋት ያለመ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የሸገር ከተማ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አበራ ጫላ ናቸው።
የጉብኝቱ ዋና ዓላማ በተለይም ምርታማነትን ለማሳደግና የተገኙ ስኬቶችን ለማስፋፋት ታልሞ መሆኑን አንስተዋል።
በጉብኝቱ ላይ የተገኙት የኮዬ ፈጬ ክፍለ ከተማ አስተዳዳሪ አቶ ለሚ ረጋሳ በበኩላቸው፤ ዘመናዊ ግብርና የኢኮኖሚ ሽግግር መሠረት መሆኑን ገልጸው፣ በዚህ ረገድ የተመዘገቡ ስኬቶችን በማስፋፋት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።