በባህር ዳር ከተማ የተገነቡ የኮሪደርና ሌሎች መሰረተ ልማቶች በጣና ፎረም ለመሳተፍ ለሚመጡ እንግዶች ምቹ የጉብኝት ዕድልን ይፈጥራሉ - ኢዜአ አማርኛ
በባህር ዳር ከተማ የተገነቡ የኮሪደርና ሌሎች መሰረተ ልማቶች በጣና ፎረም ለመሳተፍ ለሚመጡ እንግዶች ምቹ የጉብኝት ዕድልን ይፈጥራሉ
ባህርዳር፤ ጥቅምት 11/2019 (ኢዜአ) ፦ በባህር ዳር ከተማ የተገነቡ የኮሪደርና ሌሎች የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች በጣና ፎረም ለመሳተፍ ለሚመጡ እንግዶች ምቹ የጉብኝት ዕድልን እንደሚፈጥሩ ተገለጸ።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የባህር ዳር ከተማ የከተማ መሠረተ ልማት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተሻገር አዳሙ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በከተማዋ የተገነቡ የኮሪደርና ሌሎች መሠረተ ልማቶች ለቱሪዝምና ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ ናቸው።
ከበላይ ዘለቀ አውሮፕላን ማረፊያ እንደወጡ ጀምሮ እስከ አባይ ማዶ ገብርኤል ድረስ ምቹ የእግረኛና የሳይክል መንገዶች፣ መዝናኛ ስፍራዎች፣ ፓርኮች፣ ፋውንቴኖችና ሌሎች መዝናኛዎች ተገንብተዋል።
በኮሪደር ልማቱ የተገነቡት ሰፋፊ መንገዶች የጣና ሐይቅ እንዲገለጥ ከማስቻላቸውም በላይ ነፋሻ፣ ቀዝቃዛና ንጹህ አየር ወደ ከተማዋ እንዲገባ በማድረግ ለእንግዶች ምቹ የጉብኝት ጊዜ እንዲኖራቸው የሚያስችሉ ናቸው።
በተጨማሪም አዲሱ የአባይ ድልድይ፣ የባህር ዳር ከተማ ዓለም አቀፍ ስታዲየም፣ ሰፋፊ የአስፋልት መንገዶችና ሌሎች የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ተደማሪ የቱሪዝም አቅም የሚፈጥሩ ናቸው ብለዋል።
ይህም የጣና ሐይቅን፣ የአባይ ወንዝንና የባህር ዳርን የተፈጥሮ እምቅ የመስህብ ጸጋ ተዘዋውረው በመጎብኘት የቆይታ ጊዜያቸውን እንዲያራዝሙ የሚያስችላቸው መሆኑን ገልጸዋል።
የአፍሪካ መሪዎች ቤዛዊት አካባቢ በሚገኘው ፓርክም የማስታወሻ ችግኝ የሚተክሉበት ሥነ ሥርዓት በማዘጋጀት አረንጓዴ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ እንደሚደረግ አስረድተዋል።
የከተማዋ ነዋሪዎችና ወጣቶች ወደ ከተማዋ የሚመጡ እንግዶችን በኢትዮጵያዊ መስተንግዶ ተቀብሎ በማስተናገድ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ አሳስበዋል።
“በአፍሪካ የሰላም መንገዶች፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትና የጂኦፖለቲካ ለውጥ” በሚል መሪ ሐሳብ የሚካሄደው 12ኛው የጣና ፎረም ከጥቅምት 13 ቀን 2019 ዓ.ም. ጀምሮ በባህር ዳር እንደሚካሄድ ይታወቃል።