የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ከታሪካዊ እውነት እስከ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ከታሪካዊ እውነት እስከ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት
ሀዋሳ፤ ጥቅምት 11/2019 (ኢዜአ) ፦የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ከታሪካዊ እውነት እስከ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት
(በእንዳለ ደበላ)
ከጥንታዊው የአክሱም ስልጣኔ አንስቶ እስከ 1983 ዓ.ም ድረስ የባህር በር ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ፣ የጂኦፖለቲካ እና የብሔራዊ ደህንነት ጉልህ ድርሻ እንደነበረው መረጃዎች ያሳያሉ።
በዚህም የባህር በር ለወጪና ገቢ ንግድ እንቅስቃሴ ብቻ ሳይሆን የጂኦ ፖለቲካና የብሔራዊ ደህንነት ጉዳይ ጭምር ነው ማለት ይቻላል።
በህዝብ ቁጥሯና በኢኮኖሚ እንቅስቃሴዋ እያደገች የመጣችው ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር ጋር ያላት ቁርኝት ከታሪኳ፣ ከጂኦግራፊ እና ከብሔራዊ ጥቅሟና ደህንነቷ ጋር የተሳሰረ የህልውናዋ ጉዳይ ነው፡፡
አሁን ኢትዮጵያ እያነሳችው ያለው የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ የሕዝቧን የህልውናና የኢኮኖሚ ዕድገት ከማረጋገጥ አንጻር መታየት ያለበት እንጂ የሌሎች ሀገራትን ጥቅም ወይም ሉዓላዊነት የሚጋፋ አይደለም።
የእሷ የባህር በር ባለቤት መሆን ከታሪክና ከሕግ እውነታዎች ጋር የተያያዘ ነው። ለአፍሪካ ቀንድና ለዓለም አቀፍ ንግድ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ጉልህ ጠቀሜታ ያለው መሰረታዊ ጥያቄም ነው ማለት ይቻላል።
በዓለም ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ኖሯት የባህር በር የሌላት ሀገር ደግሞ ኢትዮጵያ ብቻ ናት።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት በዓለም የባህር በር የሌላቸው ሀገራት አጠቃላይ የህዝብ ቁጥራቸው 668 ሚሊዮን ሲሆን ከዚህ ውስጥ ኢትዮጵያ 20 በመቶ ወይም አንድ አምስተኛውን ድርሻ ትይዛለች።
ከሌሎቹ 43 ሀገራት ጋር ሲታይ ኢትዮጵያ የራሷ የባህር በር የነበራትና በሴረኞች ታሪካዊ ስህተት የባህር በሯን ያጣች መሆኗ ልዩ ያደርጋታል።
እስከ ኤርትራ መገንጠል ድረስ ባለው ጊዜ ኢትዮጵያ ከ1000 ኪሎ ሜትር የሚበልጥ ርዝመት ያለው የባህር በር ባለቤት ነበረች። ይሁንና የሕጋዊ ውክልና ክፍተት ባለበት ሁኔታ ኢትዮጵያ የባሕር በር አልባ እንድትሆን ተደርጋለች።
ይህ ደግሞ ኢኮኖሚያዊ፣ የጂኦ ፖለቲካዊና የደህንነት ስጋት በኢትዮጵያ ላይ እንዲደቀን አድርጓል።
ኢትዮጵያ የራሷን የባህር በር ካጣች በኋላ የወጪ እና ገቢ ንግዷን ለማካሄድ ሙሉ በሙሉ በጅቡቲ ወደብ ላይ ጥገኛ ለመሆን በመገደዷ በዓመት በቢሊዮኖች ዶላር ወጪ ለማድረግ ተገዳለች።
የራሷ ወደብ ቢኖራት ይህ ከፍተኛ መጠን ያለው ሀብት ለማህበራዊ አገልግሎትና ለመሰረተ ልማት ግንባታ በማዋል በሀገሪቷ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ጉልህ ሚና ይጫወት ነበር።
የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ በዓለም አቀፍ ህግ ሲታይም የ1982ቱ የተባበሩት መንግሥታት የባሕር ሕግ ኮንቬንሽን አንቀጽ 125 እንዳስቀመጠው ወደብ የሌላቸው ሀገራት እንዳይጎዱ፣ በጎረቤት የባሕር በር ያላቸው አገራት በኩል በነፃነት የመሸጋገር እና የወደብ መሠረተ ልማቶችን የመጠቀም መብት አላቸው።
ይህን ህግ መሰረት ባደረገ መልኩ መንግስትና መላው ኢትዮጵያዊያን ላለፉት ዓመታት የታሪክና የተፈጥሮ መብት፣ የሰጥቶ መቀበል መርህን እንዲሁም እያደገ የመጣውን የህዝብ ቁጥርና የኢኮኖሚ ጫና እንደ መከራከሪያ ምክንያት ይዘው በሰላማዊ መንገድ ኢትዮጵያን የባህር ባለቤት እንድትሆን ሲሰሩ ቆይተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አዲሱ የመደመር መንግሥት በተመሰረተበት ወቅት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ፊት ቆመው“ኢትዮጵያ መውጫና መግቢያ በር እንዲኖራት በሰጥቶ መቀበል መርህ መሰረት ተግተን እንሰራለን” ያሉትም በዚህ ምክንያት ነው።
“የኢትዮጵያ ስልጣኔ ያለ ባሕር በር እውን ሊሆን አይችልም” ሲሉም አጽንኦት ሰጥተው መናገራቸው የመደመር መንግስት ለባህር በር ባለቤትነት የተሰጠውን ትልቅ ትኩረት የሚያሳይ ነው።
ኢትዮጵያን ለዘመናት ለማተራመስ ስታሴር የቆየችው ግብጽ ኤርትራ ከኢትዮጵያ እንድትገነጠልና ኢትዮጵያም ከባህር በር እንድትርቅ ለማድረግ ያለመታከት ሰርታለች።
በግብጽ የሴራ ጡጦ ያደጉት ህገወጡ የህወሓት ቡድንና ሻዕቢያም ዛሬም ባረጀና ባፈጀ አመለካከታቸው የገፉበት ሲሆን በኢትዮጵያ ላይ በፈጸሙት ጥፋት ታሪክ ተወቃሽ ሲያደርጋቸው ይኖራል።
በሕግና በዓለም አቀፍ አሠራር መሠረት የሀገር ስትራቴጂክ ሀብቶችን አጠቃቀም እና ድንበርን የተመለከቱ ጉዳዮች በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወይም በይፋዊ ሕዝበ-ውሳኔ መወሳን ሲገባቸው ኢትዮጵያ ባህር በር ያጣችበት መንገድ ይህን የተከተለ አይደለም።
የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁሩ አቶ ዳያሞ ዳሌ፤ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸው ያላትን እውነት መሰረት በማድረግ መልሶ የባህር በር ባለቤት ለማድረግ እየተከተሉ ያሉት መንገድ አግባብ መሆኑን ያነሳሉ። በዚህም ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት ለመሆን እየተከተለች ያለውን የሰጥቶ መቀበል መርህ አጠናክራ መቀጠል እንዳለባት ነው የገለጹት።
ለዚህም ከጎረቤት አገራት ጋር የሚደረጉ ሰላማዊ፣ ሕጋዊና የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረጉ ዲፕሎማሲያዊ መንገዶችን የመጠቀም አቋም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትና መላው ህዝብ ድጋፉን ማስቀጠል እንዳለበት አንስተዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መምጣቱን የገለጹት ምሁሩ፣ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ያላትን ሕጋዊና ታሪካዊ መብት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የማሳወቁ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ይላሉ።
በአሁኑ ወቅት ሀገራችን ኢትዮጵያ በፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት ውስጥ እንደምትገኝ አስታውሰው፣ ታለቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብና ሌሎች በርካታ ታላላቅ ፕሮጀክቶች ባለቤት መሆኗ ለዚህ ትልቅ እድል ይዞ መጥቷል ይላሉ።
ኢትዮጵያ ከራሷ አልፎ አጎራባች ሀገራትን በኤሌክትሪክ ሀይል ለማስተሳሰር የጀመረቻቸው አብሮ የመልማት፣ የማደግና የመለወጥ ስራዎችን አጠናክራ በማስቀጠል ዓለም አቀፍ ተቀባይነቷንና ተጽዕኖ ፈጣሪነቷን ማጠናከር ይኖርባታል ሲሉም መክረዋል።
በዚህ ብቻ ሳይበቃ ጠንካራና ዘማነዊ ቴክኖሎጂ ባለቤት የሆነ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የመገንባቱ ሂደት ተጠናክሮ መቀጠሉ በቀጣናው ያላትን ተጽዕኖ ፈጣሪነት ያጎለብተዋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ እና ሕጋዊ አማራጮችን በመተግበር ዘላቂና አስተማማኝ የባሕር በር ለማግኘት በቁርጠኝነት የጀመረቻቸውን ሥራዎች አጠናክራ መቀጠል እንዳለባትም ነው የተናገሩት።
በአሁኑ ወቅት የህዝብ ቁጥሯ በ120 ሚሊዮን በላይ እንደደረሰ የሚነገርላት ኢትዮጵያ የባህር በር ሳይኖራት ዙሪያዋ ተቆልፎ እንዳትቆይ እየተደረገ ያለው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመዋል።