የሀገር ዋልታ - ኢዜአ አማርኛ
የሀገር ዋልታ
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 11/2019 (ኢዜአ) ፦የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በጀግንነቱና በሀገር ወዳድነቱ አልፎም በዓለም የሰላም አስከባሪነቱ በቀደምትነት የሚነሳ ጠንካራ ሰራዊት ነው።
በአፍሪካ የደኅንነት ጉዳዮች ላይ ኢትዮጵያ ጠንካራ ተሳትፎና ጉልህ ሚና እንዲኖራት የተቻለውም ጠንካራ ተቋምና ብቁ ሰራዊት በመገንባቷ መሆኑ ይታወቃል።
የመከላከያ ተቋማትን በመገንባት ረገድ በዘመናት ለውጥ የተለያዩ ፈተናዎች ቢያጋጥሙትም ሰራዊቱ ግን ጀግንነቱ፣ በሀገር ወዳድነቱና ለሰንደቁ የሚከፍለው ዋጋ ከጥንት እስካሁንም የዘለቀ ነው።
በተለይም ደግሞ ባለፉት ስምንት ዓመታት መሰረታዊ የሪፎርም ስራ በማከናወን የመከላከያ ተቋማት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ የተገነቡበትና ጠንካራ ሰራዊት የተፈጠረበት አዲስ የታሪክ ምእራፍ ላይ ይገኛል።
የሀገርን ዳር ድንበርና የግዛት አንድነት በመጠበቅ፣ በሉዓላዊነት ላይ የሚደቀኑ ማናቸውንም ስጋቶች በላቀ ብቃት የሚመክት ጠንካራ ሰራዊት ተገንብቷል። በመሆኑም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ግዙፉንና ጠንካራ የሚባለውን የሀገር መከላከያ ሰራዊት ገንብታለች።
የሀገር መከላከያ ሰራዊት በጀግንነቱ፣ ግዳጅ የመፈፀም ብቃቱና ውጊያን ከርቀት የማስቀረት ብቃቱ የተመሰከረለት በሀገር ዋልታና መከታ መሆኑን በተለያዩ ማሳያዎች መግለጽ ይቻላል። የሀገር መከታ መሆን የሚቻለው በጀግንነት ብቻ ባለመሆኑ በእውቀት፣ በቅድመ ዝግጅት፣ በቴክኖሎጂና በተቀናጀ የደኅንነት ሥራ ጭምር በመሆኑ በእነዚህ ሁሉ መመዘኛዎች ሰራዊቱ የተሟላ ቁመና እና ዝግጁነት ላይ ይገኛል።
በጥቂት ዓመታት ውስጥ በላቀ ሙያ የተካነ፣ በዲሲፕሊን የታነፀ፣ በሕግ የሚመራና የሀገሩን ሕዝብ በክብር የሚያገለግል ጠንካራ ሰራዊት ተገንብቷል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ለየትኛውም የጥቃት ሙከራ ፈጣን ምላሽ የመስጠት አቅም ያካበተ፤ ስጋቶችን አስቀድሞ በመለየት ከርቀት የማስቀረት አቅም ያለው ጠንካራ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ተገንብቷል። በመሆኑም መከላከያ ሰራዊት የሰንደቅ ዓላማው አለኝታ፣ የሀገር ዋልታና መከታ መሆኑን በተግባር ማሳየቱን ይቀጥላል።
ለዚህ ሰራዊት ተገቢውን ክብር፣ ምስጋና በመስጠት ከጎኑ መሰለፍ የዜጎች ሁሉ አደራና ሃላፊነት መሆን ይኖርበታል። የሀገር የመጨረሻ ምሽግ የሆነው ጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ሁሌም ክብርና ምስጋና ይገባዋል።