ቀጥታ፡

የጉባ ብስራቶች ለኢትዮጵያ ብልጽግና መሰረት የሚጥሉ አስተማማኝ ተቋማዊ ቁመናና አቅጣጫ ይዘዋል

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 11/2019 (ኢዜአ) ፦የጉባ ብስራቶች ለኢትዮጵያ ብልጽግና መሰረት የሚጥሉ አስተማማኝ ተቋማዊ ቁመናና አቅጣጫ ይዘው እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ታላቁ የመደመር ስትራቴጂ ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት 25 ዓመታት በሁሉም መስክ አስተማማኝ መሰረት በመጣል የብዙዎች ተምሳሌት እንደምትሆን ግብ ማስቀመጡንም ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጳጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን መመረቅ ይፋ ካደረጉ በኋላ፤ በቀጣይ ጥቂት ዓመታት በሰላሳ ቢሊዮን ዶላር የሚገነቡ ትላልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን አብስረዋል።

የጉባ ብስራቶች የኒውክሊየር ሃይል ማመንጫ፣ የማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ፣ የተፈጥሮ ጋዝ ማምረቻ፣ የነዳጅ ማጣሪያና የቤቶች ልማት ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዛሬ የኢትዮጵያ ኒውክሊየር ኃይል ኮሚሽንን የሥራ እንቅስቃሴ በጎበኙበት ወቅት፤ የኒውክሊየር ቴክኖሎጂ ለበርካታ ተቋማት ግብዓት የሚሆን መሰረታዊ ዕውቀት ነው ብለዋል።


 

በጉባ ብስራቶች ከተበሰሩ ትውልድ አሻጋሪ ፕሮጀክቶች መካከል የኒውክለር ኃይል ማመንጫ አንዱ መሆኑን ገልጸው፤ ሁሉም ፕሮጀክቶች በአስደማሚ ፍጥነት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፍያ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ ከአራት ወር ባነሰ ጊዜ እንደሚጠናቀቅ ገልጸው፤ ሁለተኛው ዙር ተከትሎ ይጀመራል ብለዋል።

የተፈጥሮ ጋዝ ማምረቻ ፋብሪካ ግንባታ የመጀመሪያው ዙር ተመርቆ ሁለተኛው ተጀምሯል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ በአስተማማኝ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

የማዳበሪያ ፋብሪካውን ከተፈጥሮ ጋዝ ጋር የሚያስተሳስር መስመር መዘርጋቱን ገልጸው፤ አሁን ደግሞ ከወደብ ጋር የሚያገናኝ ማስተላለፊያ መስመር ጀምረናል ብለዋል።

የቤቶች ግንባታን እውን ለማድረግ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እየገቡ መሆኑን ጠቅሰው፤ የሞርጌጅ ባንክ ለመፍጠር ጥናት መጠናቀቁን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር እንደመሆኗ በኒውክሊየር ቴክኖሎጂ የዘገየች ቢሆንም አሁን ላይ ያለችበት ቁመና የሚያኮራ መሆኑን ገልጸዋል።

በኒውክሊየር ቴክኖሎጂ ወረቀት ላይ ያለውን በሚታይና በሚጨበጥ ሁኔታ ፕሮጀክት መሥራት የሚያስችል ቁመና ተፈጥሯል ብለዋል።

አባቶቻችን በአንድ ክረምት አርሰው ያገኙትን ሁሉንም ከመብላት ይልቅ ለክፉ ቀን ብለው ይቆጥባሉ፤ ይህ የኢትዮጵያውያን ባህል ነው ሲሉ ገልጸዋል።

እኛም ያገኘነውን ሀብት እንደ ኒውክሊየር ቴክኖሎጂ ባሉ ለትውልድ ተሻጋሪ መሰረተ ልማቶች ግንባታ በማዋል የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን እናደርጋለን ብለዋል።

ኒውክሊየር ቴክኖሎጂ በግብርና በምግብ ራስን ለመቻል፣ በጤናው ዘርፍ ጤናማ ትውልድ ለመፍጠር፣ ኢንዱስትሪዎችን የሚያንቀሳቅስ የማይዋዥቅ ሀይል ለማቅረብ እና የሰው ሀይል አቅምን ለማጎልበት ወሳኝ በመሆኑ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ኢነርጂ የምታመርትና የምትሸጥ፣ ኢንዱስትሪዎችን የምትስብ፣ የመንገድ፣ ባቡርና የቤት መሰረተ ልማት መገንባት የምትችል መሆን አለባት ብለዋል።

የተገነባውን መሰረተ ልማት ማስተዳደር የሚችል ተቋም መገንባት የሚችል አቅም መፍጠር እንደሚገባም ገልጸዋል።

ከዚህም ባለፈ ከህግ ባሻገር ሞራል የሚገዛው፣ ሌብነትን የሚጠየፍ እየመጣ ካለው እድገት ጋር አጣጥሞ መሄድ የሚያስችል ባህል መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል።

ታላቁ የመደመር ስትራቴጂ ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት 25 ዓመታት በሁሉም መስክ አስተማማኝ መሰረት በመጣል የብዙዎች ተምሳሌት እንደምትሆን ግብ ማስቀመጡንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም