ሀገራዊ አንድነትን እና አብሮነትን የሚያጎለብቱ ተግባራትን እናጠናክራለን - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ አንድነትን እና አብሮነትን የሚያጎለብቱ ተግባራትን እናጠናክራለን
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 11/2019 (ኢዜአ) ፦የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አባል ተቋማት ሀገራዊ አንድነትን እና የህዝቦችን አብሮነት የሚያጎለብቱ ተግባራትን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታወቁ።
ተቋማቱ በ5 መሠረታዊ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ሃይማኖታዊ አስተምህሮ እና ተቋማዊ አቋም አስመልክተው በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫውም የሰውን ልጅ ክብር መጠበቅ፣ የአምልኮ ስፍራዎችንና የሃይማኖት ነፃነትን ማክበር፣ በዲጂታል ሚዲያ የሚሰራጩ የሐሰት መረጃዎችንና የጥላቻ ንግግሮችን መከላከል፣ የሴቶችና ወጣቶችን የሰላም ግንባታ ተሳትፎ ማሳደግ እንዲሁም ሀገር በቀል የግጭት አፈታት ዘዴዎችን ከሃይማኖታዊ አስተምህሮ ጋር አጣጥሞ በሥራ ላይ ማዋል በሚሉ ነጥቦች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሊቃውንት ጉባኤ ምክትል ሰብሳቢ መጋቤ ሚስጥር ፍሬስብሐት ዱባለ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ የሰውን ልጅ ማክበር የፈጠረውን ፈጣሪ ማክበር ነው፤ ፈጣሪም ሰዎች እርስ በእርስ እንዲከባበሩ ማዘዙን ጠቅሰዋል።
የዲጂታል ሚዲያን ለበጎ ዓላማ ማዋል፣ የሴቶችና ወጣቶችን የሰላም ሚና ማሳደግ እንዲሁም ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ መንገዶችን ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ማዋል እንደሚገባ አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የኡለማ ጉባኤ ጸሀፊ ሼህ መሀመድዘይን ዘሀረዲን በበኩላቸው፣ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምን ሥርዓት ማስያዝ እንደሚገባና ቴክኖሎጂውን ለመማማሪያነት መጠቀም ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል።
ለሴቶችና ወጣቶች የሰላም ግንባታ ተሳትፎ ልዩ ትኩረት መስጠትና ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸውን ሀገር በቀል የእርቅ መንገዶች ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ የወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል የውጭ ግንኙነት ዳይሬክተር ፓስተር አሸብር ከተማ፣ ዘመን አመጣሹን የዲጂታል ቴክኖሎጂ ለሰላምና ለአብሮነት ግንባታ መጠቀም እንደሚገባ አንስተዋል።
ታዳጊዎችን ስለ ማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ማስተማር እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
የሴቶችና ወጣቶችን ንቁ የሰላም ተሳትፎ ማመቻቸትና ለሀገር በቀል የግጭት መፍቻ መንገዶች ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን ረዳት ፕሬዝዳንት፣ ዲፓርትመንት ዳይሬክተር እና የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ የቦርድ አባል ፓስተር አንጋው ጌታሁን፣ የማህበራዊ ሚዲያ መረጃዎች የሕዝብን ሰላም፣ አብሮነትና አንድነት የሚያጎለብቱ መሆን እንዳለባቸው ተናግረዋል።
በሰላም ግንባታ ላይ የሴቶችና ወጣቶችን ተሳትፎ ማሳደግ እንደሚገባ አንስተው፣ በሂደቱ የሃይማኖት አባቶች ትልቅ ሚና እንዳላቸው ጠቁመዋል።
አክለውም ሀገር በቀል የግጭት አፈታት ዘዴዎች ስብራትን የሚጠግኑና ቁስልን የሚፈውሱ በመሆናቸው ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።