ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ዘመናዊ የስፖርት ማዘውተሪያ መሠረተ ልማቶች ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራት የሚያስችል የስብዕና ግንባታ አቅም እየፈጠሩ ነው

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 11/2019 (ኢዜአ) ፦የአዲስ አበባ ዘመናዊ የስፖርት ማዘውተሪያ መሠረተ ልማቶች የሕብረተሰቡን የስፖርት ባህል በማሳደግ ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራት የሚያስችል የስብዕና ግንባታ አቅም እየፈጠሩ መሆኑን የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ገለጸ።

ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ሕዝብ፤ ታላቅ ርዕይ

የአዲስ አበባ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት በሁሉም ክፍለ ከተሞች ዜጎች የሚዝናኑባቸውን የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች በማስፋፋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።


 

ይህም የስፖርት ማዘውተሪያ ውስንነትን በማስቀረት አሁን ላይ አረጋውያን፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ታዳጊዎችና ሕጻናት ሳይቀር በማለዳና በማታ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚያደርጉበትን የጋራ መድረክ ፈጥሯል።

የስፖርት ማዘውተሪያዎችም በሁሉም የዕድሜ ክልል የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች በሚፈልጉት የስፖርታዊ እንቅስቃሴ ዓይነት የሚገለገሉበትን ዕድል በመፍጠር ለስብዕና ግንባታ አይነተኛ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ።


 

የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የስፖርት ለሁሉም ቴክኒክ ባለሙያ ሳህለሚካኤል ብሩ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ከዓመታት በፊት አዲስ አበባ የስፖርት ማዘውተሪያ ውስንነት ነበረባት።

የአዲስ አበባ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማትም ዘመናዊ የስፖርት ማዘውተሪያ ማዕከላትና ስፍራዎች የሚስፋፉበትን ሁነኛ ዕድል እንደፈጠረ ገልጸዋል።

የመደመር መንግሥት ለስፖርት ማዘውተሪያ ልማት የሰጠው ትኩረት ዘመናዊና ምቹ የስፖርት ማዕከላት እንዲገነቡ በማስቻል ዜጎች እንዲገለገሉ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ዘመናዊ ስፖርት ማዘውተሪያ ማዕከላት ልማትም ታዳጊዎች፣ ወጣቶችና የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን የስፖርት ባህል በማጎልበት ለስብዕና ግንባታ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አንስተዋል።

ተተኪ ስፖርተኞችም ምቹና ጽዱ በሆኑ የስፖርት መሠረተ ልማቶች ጊዜያቸውን በማሳለፍ ተሰጥኦና ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ እያደረገ መሆኑንም አስረድተዋል።


 

በቢሮው የስፖርት ማህበራትና ውድድር ዳይሬክተር አያሌው ታደለው በበኩላቸው፤ የመዲናዋ የመሠረተ ልማት እመርታ ለስፖርት ዘርፉ ዕድገት ወሳኝ ሚና እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።

የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳዎች ማኅበረሰቡ በጠዋትም ሆነ በማታ የተለያዩ ሰዓታትን ተጠቅሞ የስፖርት እንቅስቃሴ የሚያደርግበትን ወሳኝ ዕድል ፈጥረዋል ብለዋል።

ተተኪ ስፖርተኞችን በማፍራትም የሀገር አቀፍ ቡድኖችንና ብሔራዊ ቡድኖችን ውጤታማነት ለማሳደግ አቅም እየፈጠሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።


 

መንግሥት ለስፖርት ማዘውተሪያ ልማት የሰጠው ትኩረት ዘመናዊና ደረጃቸውን የጠበቁ ማዕከላት እንዲገነቡ እያስቻለ ነው ያሉት ደግሞ በቢሮው የማዕከላትና የስፖርት ማዘወተሪያ ስፍራዎች ልማትና አስተዳደር ዳይሬክተር ብርሃኑ ረታ ናቸው።

የመዲናዋ የስፖርት ማዕከላት ግንባታም ኢትዮጵያ አህጉራዊ ውድድሮችን በብቃት ማስተናገድ የምትችልበትን ዕድል በመፍጠር ለስፖርቱ ዘርፍ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ገልጸዋል።


 

በቢሮው የስፖርት ትምህርት ስልጠና ዳይሬክተር ጎሳዬ አለማየሁ፤ የመዲናዋ የተሰናሰሉ መሠረተ ልማቶች ዜጎች የስፖርታዊና ተያያዥ እንቅስቃሴዎችን የሚያደርጉበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠራቸውን ገልጸዋል።

ይህም የሳይክልና የእግረኛ መንገዶች፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ማዕከላትን በመፍጠር የነዋሪዎችን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚያሻሽል የስፖርት ምህዳር መገንባት እንዳስቻለ ተናግረዋል።

የስፖርት ማዘውተሪያ መሠረተ ልማቶቱ ቀደም ሲል የነበሩ ውስንነቶችን በመቅረፍ በሁሉም የዕድሜ ክልል የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ደረጃውን በጠበቀ የስፖርት ሜዳ የሚዝናኑበትን ዕድል መፍጠሩንም  አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም