ቀጥታ፡

በአፍሪካ የሚስተዋሉ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችን ለመፍታት አስተማማኝና ወቅታዊ መረጃ ወሳኝ ነው

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 11/2019 (ኢዜአ) ፦በአፍሪካ የሚስተዋሉ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችን ለመፍታትና ትክክለኛ የፖሊሲ ውሳኔዎችን ለማሳለፍ አስተማማኝና ወቅታዊ መረጃ ወሳኝ ነው ሲሉ የሩዋንዳ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ዕቅድ ሚኒስትር ዩሱፍ ሙራንግዋ ገለጹ።        

የአፍሪካ ስታቲስቲክስ ኮሚሽን 10ኛ ጉባኤና የተባበሩት መንግሥታት የጂኦስፓሻል መረጃ አስተዳደር ኮሚቴ ለአፍሪካ 12ኛ ጉባኤ የጋራ የመክፈቻ መድረክ እየተካሄደ ይገኛል። 

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን እየተካሄደ በሚገኘው ጉባኤ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ፣ የኢሲኤ ዋና ጸሐፊ ክሌቨር ጋቴቴ ተገኝተዋል። 

በተጨማሪም ፖሊሲ አውጪዎች፣ የስታቲስቲክስ ባለሙያዎች፣ የልማት አጋሮችና የመረጃ ባለሙያዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የሩዋንዳ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ዕቅድ ሚኒስትር ዩሱፍ ሙራንግዋ እንዳሉት፤ የአፍሪካ ህዝብ ቁጥር ከኢኮኖሚ ዕድገት፣ ከምግብ ምርትና ከመሰረተ ልማት አቅርቦት በላይ በፍጥነት እያደገ ይገኛል።

በሚቀጥሉት 15 ዓመታት ወደ ስራ ገበያ የሚገቡ ወጣቶችንና የኢኮኖሚ አቅምን አጣጥሞ ለመሄድ የመረጃ አያያዝን ማዘመን አስፈላጊ ነው ብለዋል።  

ያለ በቂ መረጃ የሚወሰኑ ውሳኔዎች ሀገራትን ዋጋ የሚያስከፍሉ ናቸው ያሉት ሚኒስትሩ፤ የሀገራት ከፍተኛ አመራሮች፣ ፓርላማዎችና የፋይናንስ ሚኒስትሮች ለስታቲስቲክስ ልማት በቂ በጀት ሊመድቡ እንደሚገባ አመልክተዋል። 

በተለይም የስታቲስቲክስ ተቋማት ያለምንም ጣልቃ ገብነት የሚሰሩበት ምቹ ሁኔታና ነጻነት ሊኖራቸው እንደሚገባ ተናግረዋል።

ብሔራዊ የስታቲስቲክስ ተቋማት ዘመናዊ አሰራርን በመከተል የሚወጡ ብሄራዊ መረጃዎችን የሚመሩና የሚያስተዳድሩ መሆን እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

ጥራት ያለው መረጃን በወቅቱ በማቅረብ ለህዝብና ለፖሊሲ አውጪዎች ተደራሽ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

እንደ ኢሲኤ፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን እና የአፍሪካ ልማት ባንክ ያሉ ተቋማት እንዲሁም ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂና የትምህርት አጋሮች የስታቲስቲክስ ልማትን በገንዘብና በዕውቀት ለመደገፍ በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም