ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በፋይናንስና በዲጂታል ዘርፍ ውጤታማ ተግባራትን አከናውናለች - ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 11/2019 (ኢዜአ) ፦ ኢትዮጵያ በፋይናንስና በዲጂታል ዘርፍ ውጤታማ ተግባራትን ማከናወኗን የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ።

ፕሬዝዳንቱ ይህን የተናገሩት የአፍሪካ ስታቲስቲክስ ኮሚሽን 10ኛ ጉባኤና የተባበሩት መንግሥታት የጂኦስፓሻል መረጃ አስተዳደር ኮሚቴ ለአፍሪካ 12ኛ ጉባኤ የጋራ መድረክን በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት ነው።

መድረኩ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ሲሆን፤ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ፣ የሩዋንዳ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ዕቅድ ሚኒስትር ዩሱፍ ሙራንግዋና የኢሲኤ ዋና ፀሐፊ ክሌቨር ጋቴቴ ተገኝተዋል።

በተጨማሪም ፖሊሲ አውጪዎች፣ የስታቲስቲክስ ባለሙያዎች፣ የልማት አጋሮችና የመረጃ ባለሙያዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ በፋይናንስና በዲጂታል ዘርፍ ውጤታማ ስራዎች ተከናውነዋል።

ብሔራዊ የዲጂታል ክፍያ ስትራቴጂ መዘጋጀቱን፣ የፋይናንስ ዘርፉ ነፃ መደረጉንና የባንኮች የክፍያ መሠረተ ልማት መሻሻሉን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ ፕሮግራም "ፋይዳ" ከለውጦቹ አንዱ መሆኑን ገልጸው፤ ፕሮግራሙ ደኅንነቱ የተጠበቀ የኤሌክትሮኒክ ማረጋገጫ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።


 

ይህም የባንክ፣ የሞባይል ገንዘብ፣ የቴሌኮምና የሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ተደራሽነት እንደሚያሰፋም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የሀገሪቷን የስታቲስቲክስ ሥርዓት የመምራትና የማስተባበር ስራ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ኢትዮጵያ ልምዷን ለማካፈልና ከሌሎችም ለመማር ዝግጁ መሆኗንም ገልጸዋል።

የአፍሪካ ሀገራት የስታቲስቲክስ ነፃነትን እንዲያስጠብቁ፣ የሕግ ማዕቀፎችንና ተቋማትን እንዲያጠናክሩና በብሔራዊ የስታቲስቲክስ ሥርዓታቸው ላይ ኢንቨስት እንዲያደርጉም አሳስበዋል።

የጥራት ጉድለት ያለበት መረጃ መጠቀም በማስረጃ ላይ የተመሠረተ ውሳኔን እንደሚያስተጓጉል፣ ልማትን እንደሚያደናቅፍና ተጠያቂነትን እንዳይሰፍን የሚያደርግ መሆኑንም ገልጸዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የመረጃ ጥራትን ለማስጠበቅ በጋራ እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

ብሔራዊ የስታቲስቲክስ ቢሮዎችና መሪዎቻቸው ወቅታዊ መረጃ የማምረት፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የመጠቀምና አዳዲስ የመረጃ ምንጮችን የማቀናጀት ኃላፊነት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

የአፍሪካ የስታቲስቲክስ ቻርተር በ2009 በአዲስ አበባ መጽደቁን አስታውሰው፤ የአፍሪካ የስታቲስቲክስና የጂኦስፓሻል መረጃ ባለሙያዎች መድረክ በአዲስ አበባ መካሄዱ ተገቢ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም