የድጋፍ ሰልፉ ህዝቡ የጥፋት ቡድኖችን ያወገዘበትና ለዘላቂ ሰላም ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር ያሳየበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የድጋፍ ሰልፉ ህዝቡ የጥፋት ቡድኖችን ያወገዘበትና ለዘላቂ ሰላም ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር ያሳየበት ነው
ባህር ዳር ፤ ጥቅምት 11/2019 (ኢዜአ) ፦ በአማራ ክልል የተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ህዝቡ የጥፋት ቡድኖችን ያወገዘበትና ለዘላቂ ሰላም ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር ያሳየበት መሆኑን የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አስታወቀ።
በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች የሀገር መከላከያ ሰራዊትን የሚደግፍና የላቀ አክብሮት የሰጠ የድጋፍ ሰልፍ ከቀናት በፊት መካሄዱ ይታወቃል።በዛሬው ዕለትም ደቡብ ወሎ ዞን በተለያዩ ከተሞችና ወረዳዎች የሀገር መከላከያ ሠራዊትን የሚደግፍ ህዝባዊ ሰልፍ ተካሄዷል።
የድጋፍ ሰልፉ ተሳታፊዎችም የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሀገራችን ኩራትና የክብራችን መገለጫ በመሆኑ ከጎኑ ሆነን የሚጠበቅብንን ሃላፊነት እንወጣለን ሲሉ አረጋግጠዋል።
የሀገር ክብር፣ ሉአላዊነት፣ ዘላቂ ሰላምና ልማት ለሀገር እድገት ወሳኝ መሆኑን አንስተው በዚሁ መሰረት ሀገራዊ ሃላፊነታችንን እንወጣለን ብለዋል።
በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች የተካሄደውን ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ በተመለከተ ኢዜአ ያነጋገራቸው በክልሉ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል የኦፕሬሽናል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ዘለቀ አለባቸው፤ በሰልፉ ላይ ህዝቡ የሰላም አጋር መሆኑንና ከሰራዊቱ ጎን በመሰለፍ የበኩሉን ሃላፊነት የሚወጣ መሆኑን በተግባር አሳይቷል ብለዋል።
በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች በጫካ የሚንቀሳቀሱ ዘራፊና ጽንፈኛ ቡድኖች የሚያደርሱትን እንግልት በመታገልም ህዝቡ የጸጥታ ሃይሉን እያገዘ መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም በክልሉ የተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ህዝቡ የጥፋት ቡድኖችን ያወገዘበትና ለዘላቂ ሰላም ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር ያሳየበት መሆኑን ምክትል ኮሚሽነር ጀነራሉ ገልጸዋል።
በክልሉ አሁን ላይ የተፈጠረውን ሰላምና መረጋጋት በማፅናት ለማዝለቅ ፖሊስ ከተለያዩ የጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን አንስተው የህዝቡም ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።
በጫካ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የቀድሞ ታጣቂዎችም የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመቀበል ትጥቃቸውን በመፍታት ህዝቡን እየተቀላቀሉ መሆኑን ጠቅሰው ሌሎችም ይህንኑ እድል መጠቀም እንዳለባቸው አሳስበዋል።