የባህር ዳር ከተማን ለቱሪዝም፣ ለኢንቨስትመንትና ለንግድ ምቹ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች ይጠናከራሉ - ኢዜአ አማርኛ
የባህር ዳር ከተማን ለቱሪዝም፣ ለኢንቨስትመንትና ለንግድ ምቹ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች ይጠናከራሉ
ባህርዳር ፤ ጥቅምት 11/2019 (ኢዜአ) ፦ የባህር ዳር ከተማን ለቱሪዝም፣ ኢንቨስትመንትና ለንግድ ምቹ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የከተማዋ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማው ገለጹ።
የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር በ2019 በጀት ዓመት የሚያከናውነውን የመሠረተ ልማት ግንባታ ዛሬ አስጀምሯል።
በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው እንደገለጹት፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከ19 ኪሎ ሜትር በላይ የኮሪደር ልማት በማከናወን የከተማዋን እድገት ማፋጠን ተችሏል።
እየተገነቡ ያሉ የኮሪደርና ሌሎች የመሠረተ ልማት ግንባታዎችም የባህር ዳር ከተማ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን ለማስተናገድ ተመራጭ እንድትሆን ማስቻሉን ተናግረዋል።
በዛሬው ዕለትም በተለምዶ ከመድኃኒዓለም እስከ አዲሱ ድልድይ የሚገነባውን ከስድስት ኪሎ ሜትር በላይ የኮሪደር ልማት ግንባታ ማስጀመር መቻሉን ገልጸዋል።
የከተማዋን ሰላም ከማጽናት ጎን ለጎን 24 ሰዓት የልማት ፕሮጀክቶችን በማከናወን የህብረተሰቡን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማሳደግ በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
በኮሪደርና ሌሎች የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ህብረተሰቡ በጉልበቱና በገንዘቡ እያደረገ ያለው አስተዋጽኦ የሚበረታታ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ባህር ዳርን የተሞክሮ ማዕከል ለማድረግ የሚያስችሉ የመሠረተ ልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ያሉት ደግሞ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የከተማና መሠረተ ልማት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተሻገር አዳሙ ናቸው።
በዚህም ባለፉት ዓመታት የጣና ሐይቅ ዳርቻን መሠረት ያደረገ የኮሪደር፣ የአረንጓዴ መዝናኛ ስፍራና ሌሎች የልማት ሥራዎችን በማከናወን የባህር ዳርን የተፈጥሮ ውበት መግለጥ መቻሉን ተናግረዋል።
ዛሬ የተጀመረውን ከመድኃኒዓለም እስከ አዲሱ የአባይ ድልድይ ያለውን የኮሪደር ልማት በፍጥነትና በጥራት ገንብቶ ለህዝብ ጥቅም ለማዋል በትኩረት እንደሚሰራም ገልጸዋል።
በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይም የከተማዋ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶችና ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።