በነገሌ ቦረና ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጠት ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በነገሌ ቦረና ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጠት ጀመረ
ነገሌ ቦረና ፤ ጥቅምት 11/2019 (ኢዜአ) ፦በነገሌ ቦረና ከተማ አስተዳደር የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን ከ80 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጭ የተገነባው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ስራ መጀመሩን የከተማው አስተዳደር አስታወቀ።
ትልቅ አገር፣ ትልቅ ህዝብ፣ ታላቅ ርዕይ
የማእከሉ ተወካይ አቶ መሳይ ጥላሁን ለኢዜአ እንዳስታወቁት በዚህ ሳምንት ውሰጥ ስራ የጀመረው ማእከል የመንግስት ሴክተር መስሪያ ቤቶች አገልግሎቶችን በአንድ ቦታ በመስጠት የተገልጋዮችን እርካታ ለማረጋገጥ የሚያስችል ነው።
በመንግስት ኢንሼቲቭ ተግባራዊ የሆነው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለከተማው አስተዳደር አገልግሎት አሰጣጥ መዘመን ፋይዳው የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል።
ማእከሉ በተሻሻለ ቴክኖሎጂና በዘርፉ በሰለጠኑ ብቃትና ክህሎት ባላቸው ባለሙያዎች መደራጀቱ አገልግሎቱን ለማቀላጠፍ እንደሚረዳም ገልጸዋል፡፡
ዘመናዊና ፍትሐዊ መንግስታዊ የአገልግሎት አሰጣጥ በማሳለጥ አላግባብ የሚባክን ጊዜና ወጭ የሚቆጥብ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡
በዚህም የተጠያቂነት አሰራርን በማምጣት ህብረተሰቡ በመንግስት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ላይ አመኔታ እንዲኖረው አበርክቶው የጎላ መሆኑንም አብራርተዋል።
በተለይም ተገልጋዩን ለምሬት ሲዳርጉ የነበሩ ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን ለመከላከል ምቹ መደላድል እንደሚፈጥር አውስተዋል።
በቀጣይም መሰል አገልግሎቶችን በቀበሌ ደረጃ ለማስፋፋት መታቀዱን አስታውቀዋል።
ማእከሉ የባንክና የፍትህ ተቋማትን ጨምሮ የተለያዩ መንግስታዊ አገልግሎት ሰጭ ተቋማትን ያካተተ መሆኑን አክለዋል።
የከተማው ነዋሪ አቶ ጂረኛ ቀጀላ በሰጡት አስተያየት ማእከሉ ከማዘጋጃ ቤት አገልግሎት ጋር በተያያዘ በነዋሪው ላይ ሲደርስ የነበረውን እንግልት ያስቀራል ብለዋል።
ይህ አይነት አገልግሎ አካታች እና ለሁሉም ዜጋ በፍትሀዊነት ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል መሆኑንም አክለዋል።
አቶ ደመቀ ደገፋው በበኩላቸው፤ የአገልግሎት አሰጣጡ መዘመን ጊዜን ከመቆጠብ አንስቶ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።
ለተገልጋዩ ህብረተሰብ ፈጣን የአገልግሎት አሰጣጥን በመዘርጋት እርካታን ከማጎናጸፍ በዘለለ ህዝቡ ፊቱን ወደ ልማት እንዲያዞር ይረዳል ብለዋል።
ኋላ ቀር የወረቀት አሰራርን በማስቀረት በየጊዜው ቅሬታ የሚቀርብበትን የሰነድና የፋይል መጥፋት ችግር እንደሚያስቀርም ያላቸውን ተስፋ ተናግረዋል።