ቀጥታ፡

ጣና ፎረም ለቀጣናዊ ችግሮች በዕውቀት ላይ የተመሰረተ መፍትሔ የሚያስገኝ መድረክ ነው 

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 11/2019 (ኢዜአ) ፦ ጣና ፎረም ለቀጣናዊ ችግሮች በዕውቀት ላይ የተመሰረተ መፍትሔ የሚያስገኝ የሰላምና ደህንነት መድረክ መሆኑን የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግሥታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ገለጸ።

የአፍሪካን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማዕከል በማድረግ በአሕጉሪቱ ሰላምና ደህንነት ላይ የሚመክረው የጣና ፎረም ለ15 ዓመታት በስኬት ተካሂዷል።

12ኛው የዘንድሮው የጣና ፎረም ''አፍሪካን ወደ ሰላም የሚወስዱ መንገዶች፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትና የቀጣናዊ ፖለቲካዊ ሽግግር” በሚል መሪ ሐሳብ የፊታችን አርብ በባሕር ዳር ከተማ ይጀምራል።

በኢትዮጵያ የኢጋድ ተጠሪ አበባው ቢሆነኝ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን የመንግሥትነት ታሪክ፤ ቅኝ ያልተገዛች፣ የተለያዩ ዓለም አቀፍና ቀጣናዊ ተቋማት መገኛ ናት።

ኢትዮጵያ የታላቁ ወንዝ ዓባይ መነሻ፣ የጣና ሰገነት፣ በአፍሪካ ሁለተኛው ግዙፍ ህዝብ፣ የዓለም የዲፕሎማሲ መናኽሪያ መሆኗን ገልጸው፤ የጣና ፎረምን አዘጋጅ ሀገር መሆኗ የተገባ ነው ብለዋል።


 

የጣና ፎረም በአፍሪካ ሰላምና ደህንነት ላይ በመምከር አማራጭ የፖሊሲ ሀሳቦችን የሚያፈልቅ ግዙፍ መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢጋድ ቀጣና ግጭት፣ አለመረጋጋትና በርካታ የፀጥታ ችግሮች የሚታዩበት መሆኑን ገልጸው፤ ጣና ፎረም ለቀጣናዊ ችግሮች በዕውቀት ላይ የተመሰረተ መፍትሔ ሀሳብ ማስገኘቱን ገልጸዋል።

የጣና ፎረም የሀገራት መሪዎች፣ የፖሊሲ ጥናት ተቋማት፣ ምሁራን፣ የቀድሞ መሪዎችና ወጣቶች እንደሚሳተፉበት ገልጸው፤ ኢጋድ ፎረሙን ይደግፋል፤ ያበረታታል ብለዋል።


 

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ደህንነት ጥናት ተቋም ዳይሬክተር ሜርሲ ፍቃዱ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ጣና ፎረም በአፍሪካ የሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ላይ የሚመክር መሆኑን ገልጸዋል።

የጣና ፎረም መሪዎች በቀጣናው የፀጥታ ጉዳይ ላይ በጥልቀት የሚነጋገሩበትን ነፃ መድረክ እንደሚፈጥር ገልጸው፤ የፎረሙ ግብዓት ለአህጉራዊ ሰላምና ደህንነት ሥራ ያገለግላል ብለዋል።

አፍሪካውያን ራሳቸው አጀንዳ የሚቀርጹበት አፍሪካዊ ፎረም ነው ያሉት ዳይሬክተሯ፤ ጣና ፎረም ፖሊሲ አውጭዎችና ውሳኔ ሰጭዎች በግልጽ የሚነጋገሩበትን ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

ጣና ፎረም ኢትዮጵያ ለአፍሪካውያን የምታበረክተው የሰላም ስጦታ መሆኑን ገልጸው፤ ኢትዮጵያ መድረኩን ከማዘጋጀት ባለፈ ለፎረሙ ተሳታፊ መሪዎች ጥሪ ታደርጋለች ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም