የኢትዮጵያ ኒውክሊየር ኃይል ኮሚሽን ለኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ የልማት ርዕይ ከፍተኛ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ አለው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ኒውክሊየር ኃይል ኮሚሽን ለኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ የልማት ርዕይ ከፍተኛ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ አለው
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 11/2019 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ ኒውክሊየር ኃይል ኮሚሽን ለኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ የልማት ርዕይ ከፍተኛ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ አለው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ኒውክሊየር ኃይል ኮሚሽንን መጎብኘታቸውን አስታውቀዋል።
ጉብኝታቸውን አስመልክተው በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፦ይህ ተቋም ለኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ የልማት ርዕይ ከፍተኛ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።
ኢትዮጵያ እጅግ ከፍተኛ በሆነ እምቅ አቅሟ እና በተትረፈረፈ ተፈጥሯዊ ሀብቷ ለረጅም ጊዜ ትታወቃለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲሱ ምዕራፍ ደግሞ እነዚህን ሀብቶች ወደ ተጨባጭ ልማት፣ የቴክኖሎጂ እድገት እና ወደ ጋራ ብልጽግና መለወጥ ላይ እንደሚያተኩር አስታውቀዋል።
አስተማማኝና ዘላቂ የኃይል አቅርቦት ለኢንዱስትሪ፣ ለማኑፋክቸሪንግ፣ ለዲጂታል መሠረተ ልማትና ለአጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ሽግግር ማዕከላዊ ሚና አለውም ብለዋል።
የኒውክሊየር ቴክኖሎጂ ደግሞ የኃይል ዋስትናን በማጠናከር እየገሰገሰ ያለውን ፍላጎት ለማሟላት ትልቅ ዕድል የሚፈጥር ከመሆኑም በላይ፤ ከኃይል ምርት ባለፈ በጤና፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በአካባቢ ጥበቃ ዘርፎች ለሀገራዊ ልማትና ለቴክኖሎጂ አቅም ግንባታ መሠረታዊ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ኒውክሊየር ኃይል ኮሚሽን ለብሔራዊ የኒውክሊየር ኃይል ፕሮግራም አስፈላጊ የሆኑትን ተቋማዊ እና ቴክኒካዊ መሠረቶች በመጣል ይህንን ርዕይ ለማሳካት ስትራቴጂካዊ ሚና አለው ብለዋል።
ብቁ የሰው ኃይል ማፍራት፣ ሳይንሳዊ ምርምርን ማስፋፋት እና የተቋሙን ዕውቀት ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ ወሳኝ ተግባራት መሆናቸውንም አንስተዋል።
ይህም ብሔራዊ አቅምንና ልዩ ሙያዊ ብቃትን በማዳበር የኒውክሊየር ኃይል ልማት ሰላማዊ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ አስተማማኝ እና ዘላቂ በሆነ መንገድ በኃላፊነት ስሜት እንዲከወን እንደሚያደርግ ገልጸዋል።