በደቡብ ወሎ ዞን ለመከላከያ ሠራዊት ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ወሎ ዞን ለመከላከያ ሠራዊት ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ እየተካሄደ ነው
ሀርቡ ፤ ጥቅምት 11/2019 (ኢዜአ) ፦በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን በተለያዩ ከተማ አስተዳደሮችና ወረዳዎች የሀገር መከላከያ ሰራዊትን የሚደግፍ ህዝባዊ ሰልፍ እየተካሄደ ነው።
ሰልፉ እየተካሄደ የሚገኘው በሃርቡ፣ በጊምባ፣ በሐይቅ፣ በቃሉ፣ በኩታበርና በሌሎች ከተሞች ነው።
አደባባይ የወጡ ሰልፈኞችም «መከላከያ ሰራዊታችን ለህዝቦች ክብርና አንድነት! መከላከያ ሰራዊታችን የህብረ ብሔራዊነታችን ማሳያ አርማችን ነው!» የሚሉና ሌሎች መፈክሮችን እያሰሙ ይገኛሉ።
በተጨማሪም «በማይነጥፈው የመከላከያ ሰራዊታችን የጀግንነትና የተጋድሎ ታሪክ የሀገራችንን ክብር ከፍ እናደርጋለን፤ የሀገራችንን ሰላም ለማወክ ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር የተሰለፉ ሃይሎችን በፅኑ እናወግዛለን» የሚሉ መልዕክቶች እየተላለፉ ነው።
«መንግስት ለሰላም መስፈን የሚወስዳቸውን እርምጃዎች እንደግፋለን፤ የኢትዮጵያ ጠላቶችን እየደመሰስን ሰንደቅ ዓላማችንን ከፍ እናደርጋለን» የሚሉ መፈክሮችም ተካተውበታል።
«ፅንፈኛና ተላላኪዎች ከባዕዳን ተልዕኮ ወስደው ኢትዮጵያን በሚወጉት ላይ የሚወሰደውን እርምጃ እንደግፋለን» ሲሉ በመፈክሮቻቸው ገልጸዋል።
በሰልፉ ላይ ነዋሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና ሌሎችም እየተሳተፉ ይገኛሉ።