የአፍሪካ ነፃነት ክብራቸውን አሳልፈው በማይሰጡ ዜጎች የተገኘ ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ነፃነት ክብራቸውን አሳልፈው በማይሰጡ ዜጎች የተገኘ ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ጥቅምት 10/2019 (ኢዜአ)፦የአፍሪካ ነፃነት በስጦታ የተቸረ ሳይሆን ክብራቸውን አሳልፈው በማይሰጡ ዜጎች የተገኘ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኬንያ፣ ኤልዶሬት በተከበረው የማሹጃ ቀን (የጀግኖች ቀን) ብሔራዊ በዓል ላይ ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በዚሁ መልዕክታቸው፤ ለሀገራቸው ነፃነት ለታገሉና ሉዓላዊነታቸውን ለማስከበር ታላቅ መስዋዕትነት ለከፈሉ የኬንያ ጀግኖች ያላቸውን ታላቅ አክብሮት ገልጸዋል።
እ.ኤ.አ. በጥቅምት 1952 የቅኝ ግዛት ባለሥልጣናት ጆሞ ኬንያታን እና አምስት አብረዋቸው የነበሩ መሪዎችን ማሰራቸውን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የእነርሱ መታሰር የትግሉ መስፋፋት ዋነኛ ምልክት በመሆን ስፍር ቁጥር የሌላቸው ኬንያውያን ትግሉን በመቀላቀል ወደፊት እንዲያስቀጥሉት አድርጓል ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን በዓድዋ ከሁሉም የአገሪቷ ማዕዘናት በመምጣትና በአንድነት በመቆም የአገራቸውን ሉዓላዊነት ማስከበር መቻላቸውንም አስታውሰዋል።
የአፍሪካ ነፃነት በስጦታ የተቸረ አይደለም፤ ክብራቸውን አሳልፈው በማይሰጡ ዜጎች የተገኘ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህንን ነፃነት በአደራ የተሰጠ፣ ለቀጣዩ ትውልድ የሚተላለፍ እንዲሁም ለእያንዳንዱ ዜጋ ዕድል የሚፈጥር በማድረግ ልንለውጠው ይገባል ብለዋል።
በዚህም ዛሬ የኬንያ ጀግኖች መምህራንን፣ ነርሶችን፣ አርቲስቶችን፣ አትሌቶችን እና ሥራ የሚፈጥሩ ዜጎችን ይጨምራሉ ሲሉ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያና የኬንያ አትሌቶች ጎን ለጎን ይሮጣሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አንዳንድ ጊዜ ኬንያ፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ኢትዮጵያ ቢያሸንፉም፣ በአንድነት አፍሪካ ምን ማሳካት እንደምትችል በጋራ ለዓለም አሳይተዋል ብለዋል።
በዚህም እንደ ተቀናቃኝ እየተወዳደሩ፣ እንደ አጋር እንደሚገነባቡ ገልጸው፤ በኢትዮጵያ ይህንን መንፈስ «መደመር» እንለዋለን ብለዋል።
መደመር ለአንድ ዓላማ ጥንካሬዎቻችንን የምናሰናስንበት ሕብረት ማለት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህም ኢትዮጵያና ኬንያን ባስተሳሰረው የኤሌክትሪክ ኃይል ፕሮጀክት በግልጽ እንደሚታይ ተናግረዋል።
እ.ኤ.አ. ከ2022 ወዲህ ኢትዮጵያ ለኬንያ ንጹህ ኃይል እያቀረበች መሆኑን ገልጸው፤ ይህም ለቤቶች ብርሃንን፣ ለኢንዱስትሪም ኃይልን ሰጥቷል ብለዋል።
ይህ አጋርነት በንግድ ሥራዎችም በኩል እያደገ መምጣቱን በመግለጽ፣ የሳፋሪኮምን በኢትዮጵያ አገልግሎት መስጠት መጀመር ለአብነት አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያንና ኬንያን መልክዓ ምድር ጎረቤታሞች፣ ታሪክ ደግሞ ወንድማማቾች አድርጎናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ምርጫዎቻችን ብልጽግናን እውን ማድረግ የሚያስችሉን መሆን አለባቸው ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት የሁለቱም ሀገራት አርሶ አደሮችና አምራቾች በድንበር በኩል በቀላሉ መገበያየት መቻል እንደሚኖርባቸው አመልክተው፤ በሕዝቦች መካከል የባህል ትውውቅ ማድረግ ይገባል ብለዋል።