የህብረ-ብሔራዊ አንድነት ጠንካራ መገለጫ - የሀገር መከላከያ ሰራዊት - ኢዜአ አማርኛ
የህብረ-ብሔራዊ አንድነት ጠንካራ መገለጫ - የሀገር መከላከያ ሰራዊት
ሙሴ መለሰ
የሀገር መከላከያ ሠራዊት ኢትዮጵያን በሚወክል መልኩ የተደራጀ በጠንካራ ዲሲፕሊን የተገነባ የሀገር ሉዓላዊነት ጥግ ነው። ዋነኛ መገለጫውና ጥንካሬውም ከማኅበረሰቡ የወጣና ለሕዝብ ዘላቂ ደኅንነት የቆመ መሆኑ ጭምር ነው።
ሠራዊቱ የሀገር ሉዓላዊነትን ከማስከበርና ወታደራዊ ግዳጆችን በብቃት ከመወጣት ባለፈ፣ በሰላሙ ጊዜም ቢሆን ማኅበረሰቡን በቀጥታ የሚጠቅሙ በርካታ ሕዝባዊና ልማታዊ ስራዎች ላይ በስፋት በመሳተፍ ላይ ይገኛል። ይህ ዓይነቱ ሁለንተናዊ ተሳትፎው መሠረቱ ህዝባዊነቱ መስዋዕትነቱም ለሃገራዊ ሉዓላዊነቱ መሆኑን የሚያሳይም ነው።
የወገን አለኝታ የህዝብ መከታ ጋሻም ነው ። ሀገሩን ከወራሪ ጠላት ወገኑን ከጥቃት የሚከላከል ፤ በችግሩ ጊዜም ፈጥኖ የሚደርስ ከስንቁ የሚያካፍል ለወገኑ የሚሰዋ የሚቆስልም ጭምር ። ሕዝባዊ ወገንተኛነቱ በተለይም በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ወቅት ፈጣንና ውጤታማ ምላሽ በመስጠት ረገድ በግልጽ ይንጸባረቃል። ሠራዊቱ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚከሰቱ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮችን ተከትሎ ፈጥኖ ለወገኑ የሚደርስም ነው።
ከዚህ በተጨማሪ፣ ሠራዊቱ በሀገሪቱ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና አረንጓዴ ልማትን ለማፋጠን በሚደረጉ ዘመቻዎች ውስጥ ግንባር ቀደም ተዋናይ ነው። በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢዎች በሚከናወኑ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ሁሉ ጠንካራ ህዝባዊ አጋርነቱ የማይለይ መሆኑን ዘወትር ያረጋግጣል።
ጀግናው የሃገር መከላከያ ሠራዊት በሀገር ላይ ባዳም ባንዳም ፣ ላኪም ተላላኪም ተዛዝለው እሳት ይዘው ቢመጡ ጠንካራ ክንዱን በማቅመስ ሃገርና ህዝብን የመጠበቅ ቃልኪዳኑን ሁሌም የሚያስመሰክረው የሰርክ ተግባሩ ነው። በሰላሙ ጊዜ ደግሞ በጉልበቱም በሃብቱም በቴክኖሎጂውም በእውቀቱም በመታገዝ የህዝብን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጡ የልማት ስራዎች ግንባር ቀደም ተሳታፊ መሆኑም የተለመደ ነው።
የሀገሪቱን ግዙፍ ብሔራዊ የልማት ፕሮጀክቶች በአስተማማኝ ሁኔታ ከመጠበቅ ባሻገር፣ የሠራዊቱ ዘመናዊ የምህንድስና፣ የሳይንስና የሕክምና ተቋማት ለሕዝባዊ አገልግሎት በስፋት እየዋሉም ይገኛሉ።
ይህ በሰላምና በልማት ስራዎች ላይ የተመዘገበው ደማቅ አሻራው፣ የጦር ግንባር ጀግና ብቻ ሳይሆን፣ የሀገር ግንባታ ዋስትናና የሕዝብ አለኝታ መሆኑን በተሟላ ሙያዊ ብቃት ያረጋገጠበት እሴቱም ነው።