ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ እና ኬንያ የወደፊት ትብብር በመደመር ፍልስፍና ላይ የተመሰረተ ሊሆን ይገባል

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 10/2019 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያና የኬንያ የወደፊት ዕጣ ፈንታ በመደመር ፍልስፍና እና የጋራ ልማት መርህ ላይ የተመሰረተ መሆን እንዳለበት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

በኬንያ የማሹጃ ቀን (የጀግኖች ቀን) ዛሬ ተከብሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዚህ ብሔራዊ ክብረ በዓል ላይ በመገኘት ንግግር አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ለኬንያ ነፃነት እና ሉዓላዊነት መከበር ህይወታቸውን ለከፈሉ የነፃነት ታጋዮች ከፍተኛ ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን ያላቸውን ታላቅ ክብር ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኬንያውያን የነፃነት ተጋድሎ ከኢትዮጵያውያን የ1888ቱ የዓድዋ ድል ታሪክ ጋር የሚመሳሰል መሆኑን ገልጸው፣የዓድዋ ድል መላው ኢትዮጵያውያን ከአራት ማዕዘን ተመው ሀገራቸውን በአንድነት ያስከበሩበት ታላቅ ታሪካዊ ክስተት መሆኑን አውስተዋል።


 

የአፍሪካ ነፃነት በስጦታ የተበረከተ ሳይሆን፣ በሕዝቦች መስዋዕትነት፣ ጽናትና በጽኑ ወንድማማችነት የተገኘ ታላቅ ድል ነው ብለዋል።

የሁለቱ ሀገራት የተሳሰረ ታሪክ የወደፊቱን የጋራ ጉዞ መምራት እንዳለበት የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣በመደመር እሳቤ አማካኝነት በታዳሽ ኢነርጂ፣ በድንበር ተሻጋሪ የመሰረተ ልማት ትስስር፣ በቴሌኮሙኒኬሽንና በንግድ ዘርፍ የሚከናወኑ የጋራ ስራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል።

የሁለቱን ሀገራት የንግድና የኢኮኖሚ ትስስር በተመለከተ፣ አርሶ አደሮችና አምራቾች በድንበር በኩል ያለ ምንም እንቅፋት በነፃነት መነገድ የሚያስችላቸው ምቹ ሁኔታዎች ሊፈጠሩላቸው እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

በንግድና አገልግሎት ዘርፍ እየታየ ያለውን እድገት ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኬንያው የቴሌኮም ኩባንያ ሳፋሪኮም በኢትዮጵያ ገበያ በመግባት የቴሌኮም እና የኤም-ፔሳ (M-Pesa) የፋይናንስ አገልግሎትን በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵውያን ተደራሽ ማድረጉን ጠቅሰዋል።


 

በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣ በሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች መካከል ያለውን ወንድማማችነትና ማህበራዊ ትስስር ለማጠናከር የጉዞና የባህል ልውውጦች በስፋት ሊጎለብቱ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የቀደሙት ትውልዶች የከፈሉት የነፃነት መስዋዕትነት ለሁሉም ዜጎች የተሻለ የስራ እና የዕድገት እድልን ወደ መፍጠር መለወጥ እንዳለበትና ይህም የወቅቱ ትውልድ ዋነኛ ኃላፊነት መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ እና ለኤልዶሬት ከተማ ሕዝብ ለተደረገላቸው አቀባበል ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም