ኢትዮጵያና ኬንያ በጋራ ታሪክና ብልፅግና መንገድ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና ኬንያ በጋራ ታሪክና ብልፅግና መንገድ
ኢትዮጵያና ኬንያ በረዥም የድንበር መስመር ብቻ የተገናኙ ጎረቤቶች አይደሉም፤ የታሪክ፣ የነፃነት፣ የጀግንነትና የጋራ ብልፅግና ራዕይ ያስተሳሰራቸው አህጉራዊ አጋሮች እንጂ።ሁለቱ ሀገራት በአትሌቲክስ የዓለም አደባባይ የነገሱ አናብስትና ለሀገራቸው ክብር ሲሉ ሕይወታቸውን አሳልፈው የሰጡ የነፃነት ታጋዮች መፍለቂያዎች ናቸው።
ሁለቱ ሀገራት በአትሌቲክስ ስፖርት የዓለምን መድረክ የተቆጣጠሩ ሯጮችና ለሀገራቸው ክብርና ነፃነት ሲሉ ሕይወታቸውን አሳልፈው የሰጡ የጀግኖች ምድር በመሆናቸው በብዙ መንገድ ይመሳሰላሉ።
ይህንን ዘመናት የተሻገረ ወዳጅነትና ስትራቴጂያዊ አጋርነት ይበልጥ የሚያጎላው ደግሞ ዛሬ በኬንያ ኤልዶሬት ከተማ በተካሄደው የጀግኖች ቀን (Mashujaa Day) በዓል ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በክብር እንግድነት ተገኝተው ያስተላላፉት ታሪካዊ መልዕክት ነው።
የሁለቱ ሀገራት ትስስር ከዘመናዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ቀደም ብሎ በድንበር አካባቢ ማኅበረሰቦች የንግድ፣ የእንስሳት እርባታና የማኅበራዊ መስተጋብር የተጣለ ጠንካራ መሠረት አለው።
በቅኝ ግዛት ዘመንም ቢሆን የኬንያ «ማዎ ማዎ» የነፃነት ታጋዮች ከኢትዮጵያ ያገኙት ድጋፍ ሁለቱ ሀገራት በጋራ ዓላማ መቆማቸውን ማሳያ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በበዓሉ ላይ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት፣ እ.አ.አ በ1952 ጆሞ ኬንያታና አምስት የነፃነት አባቶች ቢታሰሩም የኬንያ ሕዝብ ትግሉን አጠናክሮ ቀጥሏል።
ይህ የጽናት ታሪክ ኢትዮጵያውያን በዓድዋ ካስመዘገቡት ድል ጋር የተሳሰረ ሲሆን፣ የአፍሪካ ነፃነት በስጦታ የተገኘ ሳይሆን ክብራቸውን ለማስጠበቅ በጽናት የታገሉ ሕዝቦች የተጎናጸፉት የጋራ ድል መሆኑን ያሳያል።
በስፖርቱ ዓለምም ቢሆን የሁለቱ ሀገራት አትሌቶች ጎን ለጎን እየሮጡና ትከሻ ለትከሻ እየተፎካከሩ የአፍሪካን ታላቅነት ለዓለም መስክረዋል።ድሉ አንዳንዴ የኢትዮጵያ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ የኬንያ ቢሆንም፣ ሁለቱም ሀገራት የአፍሪካን አሸናፊነትና ታላላቅ ግቦችን የማሳካት አቅም ለዓለም አሳይተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በውድድር መድረክ እንፎካከራለን፤ እንደ አጋርነታችን ደግሞ ሀገሮቻችንን እንገነባለን ሲሉ የገለጹትም፣ ይህ ዓይነቱ የመደመር እሳቤ አቅምን ለጋራ ዓላማ ማዋል መሆኑን በማስገንዘብ ነው።
ዛሬ ላይ ይህ ታሪካዊ ትስስር ወደ ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ፕሮጀክቶች ተሸጋግሯል።
ኢትዮጵያ ከታዳሽ ኃይል የምታመነጨውን ኤሌክትሪክ ወደ ኬንያ እየሸጠች ሲሆን፣ ከሞምባሳ እስከ ሀዋሳ የሚዘልቀው የመንገድ ኮሪደር ደግሞ የሁለቱን ሀገራት ንግድና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እያቀላጠፈ ነው።
በተጨማሪም የሳፋሪኮም በኢትዮጵያ በስፋት መስራትና የኤም-ፔሳ የዲጂታል ክፍያ አገልግሎት መስፋፋት የሁለቱን ሀገራት የንግድና የኢንቨስትመንት ግንኙነት አዲስ ደረጃ ላይ አሸጋግሮታል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና በፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ መካከል ያለው የቅርብ የመሪዎች ግንኙነትና የተቋማት ትብብር፣ ለድንበር አካባቢ ማኅበረሰቦች ልማት፣ ለወጣቶች የሥራ ዕድልና ለድንበር ተሻጋሪ ንግድ መስፋፋት ትልቅ ዕድል ፈጥሯል።
የምሥራቅ አፍሪካና የአፍሪካ ቀንድ የጸጥታ ሁኔታ ድንበር ዘለል ትኩረትን የሚሻ በመሆኑ፣ የኢትዮጵያና የኬንያ ጥንካሬ ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ወሳኝ መሠረት ሆኖ ያገለግላል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጂኦግራፊ ጎረቤታሞች አድርጎናል፤ ታሪክ ወንድማማቾች አድርጎናል፤ የምንወስዳቸው ውሳኔዎች ደግሞ በጋራ ብልፅግና የተመሠረቱ አጋሮች ሊያደርጉን ይገባል ሲሉ የመጪውን ጊዜ አቅጣጫ አመላክተዋል።
በአጠቃላይ፣ ኢትዮጵያና ኬንያ የትናንት ታሪካቸውን እያከበሩ፣ ዛሬን በጋራ በመገንባትና ነገን በተስፋ በመቃኘት አፍሪካዊ አንድነትንና የጋራ ብልፅግናን የሚያረጋግጥ ጠንካራ የጉርብትና አርአያነታቸውን አጠናክረው ቀጥለውበታል።