ሀላባ ከተማ እና ፋሲል ከነማ አቻ ተለያዩ - ኢዜአ አማርኛ
ሀላባ ከተማ እና ፋሲል ከነማ አቻ ተለያዩ
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 10/2019 (ኢዜአ) ፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሶስተኛ ሳምንት ሀላባ ከተማ እና ፋሲል ከነማ ያደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል።
በሀላባ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ጋናዊው ካሌብ አማንክዋህ በ12ኛው ደቂቃ ሀላባን መሪ ያደረገችውን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።
ቤኒናዊው ሮማሪክ ዲንሆ አሞውሱ በ49ኛው ደቂቃ ለፋሲል ከነማ የአቻነቷን ግብ ከመረብ ላይ አስቆጥሯል።
አዲስ አዳጊው ሀላባ ከተማ በአምስት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን የያዘ ሲሆን በዘንድሮው የውድድር በሁለት ጨዋታዎች እየመራ አቻ ወጥቷል።
አንድ ተስተካካይ መርሐ ግብር ያለው ፋሲል ከነማ በሁለት ነጥብ 10ኛ ደረጃን ይዟል።
በአራተኛ ሳምንት ሀላባ ከተማ ከወላይታ ድቻ እና ፋሲል ከነማ ከሀዲያ ሆሳዕና ይጫወታሉ።
ዛሬ አስቀድሞ በተደረገ የሶስተኛ ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሸገር ከተማን 1 ለ 0 አሸንፏል።
የሶስተኛ ሳምንት መርሐ ግብር እስከ ጥቅምት 12 2019 ዓ.ም ይቆያል።