በክልሉ የተጀመሩ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን በፍጥነትና በጥራት ለማጠናቀቅ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የተጀመሩ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን በፍጥነትና በጥራት ለማጠናቀቅ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው
ዲላ፤ጥቅምት 10/2019 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በግንባታ ላይ የሚገኙ የመንገድና የድልድይ መሰረተ ልማቶችን በጥራትና በፍጥነት አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት አስተዳደር ቢሮ ገለጸ።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ንጋቱ ዳንሳ እና ሌሎች አመራሮችና ባለሙያዎች በጌዴኦ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች በግንባታ ላይ የሚገኙ የገጠር መንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን ጎብኝተዋል።
በዲላ ዙሪያ ወረዳ አንዲዳ-ሺጋዶ-ኦቲልቾ-ሄሬቤ 22 ኪ.ሜ የመንገድ ግንባታ እና የጫቢቻ ጪጩ ወንዝ 42 ሜትር ድልድይ እንዲሁም በይርጋጨፌ ወረዳ የ48 ኪሎሜትር ቡድቅሳ- ረሳ- ቱሊሴ የመንገድ ልማት ስራዎች ከተጎበኙት ፕሮጀክቶች መካከል ይጠቀሳሉ።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ንጋቱ ዳንሳ፤ የፕሮጀክቶቹ የግንባታ ሂደት በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን ተመልክተናል ብለዋል።
በመሆኑም በጥራትና በፍጥነት በማጠናቀቅ ለአገልግሎት እንዲበቁ ሌት ተቀን በመትጋት መሰራት እንደሚገባ አንስተው ለስራው አስፈላጊው ድጋፍና እገዛ የሚደረግ መሆኑን ተናግረዋል።
በ90 ቀናት አጠናቆ ለትራንስፖርት ክፍት የማድረግ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አንስተው የመስክ ምልከታውም ይህንኑ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች የተጀመሩ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን በፍጥነትና በጥራት በማጠናቀቅ ለአገልግሎት እንዲበቁ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ይገኛልም ብለዋል።
የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ መስፍን ደምሴ(ዶ/ር)፤ በዞኑ እየተገነቡ የሚገኙ የመንገድና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በይርጋጨፌ ወረዳ እየተገነባ የሚገኘው የ48 ኪሎ ሜትር ቡድቅሳ- ረሳ- ቱሊሴ የመንገድ ፕሮጀክት የ42 ኪሎ ሜትሩ ግንባታ ተጠናቆ ቀሪውን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።