ቀጥታ፡

በደቡብ፣ በደቡብ ምስራቅ እና በምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች የተሻለ የዝናብ ስርጭት ይኖራል

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 10/2019 (ኢዜአ) ፦ በቀጣዮቹ 10 ቀናት በደቡብ፣ በደቡብ ምስራቅ እና በምዕራብ የኢትዮጵያ ክፍሎች የተሻለ የዝናብ ስርጭት እንደሚኖር የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ኢኒስቲትዩቱ ከጥቅምት 11 እስከ 21 2019 ዓ.ም የሚኖረውን የአየር ሁኔታ ትንበያ ይፋ አድርጓል።

በዚሁ መሰረት በእነዚህ ቀናት በሚኖረው የአየር ሁኔታ ትንበያ፣ አሁን ከሚታዩትና በቀጣይነትም የተተነበዩት የትንበያ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ዝናብ ሰጭ የአየር ሁኔታ ክስተቶች በደቡብ፣ ደቡብ ምስራቅ፣ ደቡብ ምዕራብ፣ በምዕራብና በምስራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ከሳምንቱ አጋማሽ ጀምሮ የተሻለ ገጽታ እንደሚኖራቸው ተገልጿል።

በመሆኑም በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት የጉጂ፣ ምስራቅ ጉጂ፣ ቦረና፣ ምስራቅ ቦረና ዞኖች፤ የሲዳማ ክልል ዞኖች፤ የሶማሌ ክልል ደቡባዊ ዞኖች፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች ላይ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖራቸው አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በተጨማሪም በፀሀይ ሀይል ታግዘው ከሚጠናከሩት የደመና ክምችቶች ላይ በመነሳት ደቡብ ምዕራብ እና ደቡብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ አልፎ አልፎ በሚኖሩት ቀናት በ24 ሰዓት ውስጥ ከ11 እስከ 30 ሚሊ ሜትር የሚደርስ ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በሌላ በኩል በሚኖሩት ቀናት አልፎ አልፎ ሰሜን ምዕራብ እና በሰሜን የሀገሪቱ አካባቢዎች ወቅቱን ያልጠበቀ ቀላል መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ የኢንስቲትዩቱ መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም