የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄን ለማሳካት የተጀመረውን የተቀናጀ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ማስቀጠል ያስፈልጋል - ኢዜአ አማርኛ
የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄን ለማሳካት የተጀመረውን የተቀናጀ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ማስቀጠል ያስፈልጋል
ሚዛን አማን፤ጥቅምት 10/2019 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄን ማሳካት የብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ በመሆኑ የተጀመረውን የተቀናጀ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ማስቀጠል ይጠይቃል ሲሉ የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።
የትውልዶች ጥያቄ የሆነውን የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት ማረጋገጥ የጋራ ጥረትን የሚጠይቅ የብሔራዊ ጥቅም እና የሕልውና ጉዳይ መሆኑንም ምሁራኑ አመልክተዋል።
ኢዜአ ከሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጋር ባደረገው ቆይታ፤ የባሕር በርን ማሳካት ከዓድዋ ድል እና ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ በኋላ ትውልዱ ሦስተኛውን ደማቅ ታሪክ የሚሠራበት መሆኑን ጠቁመዋል።
በባሕር በር ጉዳይ መላው ሕዝብ ብሔራዊ ጥቅሙን ለማረጋገጥ በንቃትና በአንድነት የጀመረውን ጥረት ማጠናከር እንዳለበትም ምሁራኑ ተናግረዋል።
በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካል ሳይንስ መምህር መላኩ መሸሻ እንደገለጹት፣ ለኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት የቅንጦት ሳይሆን የሕልውና ጉዳይ ነው።
በፍጥነት እያደገ የመጣውን የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ይበልጥ ለማሳለጥና ኢትዮጵያ በየዓመቱ ለወደብ ኪራይና ለሎጂስቲክስ የምታወጣውን ከፍተኛ ወጪ በመቀነስ ለሌሎች የልማት ሥራዎች እንድታውል ያስችላታል ብለዋል።
የባሕር በር ጉዳይ ብሔራዊ ደኅንነትን የማረጋገጫ መንገድ ጭምር መሆኑንና ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ ፖለቲካ ድንገተኛ ጫናዎች ራሷን ለመጠበቅ እንደሚያስችላት ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎት የማንንም ሉዓላዊነት የመጋፋት ዓላማ የሌለውና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የታሪክና ቅርስ አስተዳደር መምህር አጥናፉ ምትኩ ናቸው።
ፍትሐዊነትን መሠረት ያደረገውና ዲፕሎማሲያዊ መርህን የተከተለው የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ፣ ዓለም አቀፍ የባሕር ሕግና መርሆዎችን መሠረት አድርጎ በጋራ መጠቀምን ያለመ መሆኑን አመልክተዋል።
ይህ በጋራ ማደግ እና በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሠረተው አካሄድ ለቀጠናው ሀገራትም አዲስ የኢኮኖሚ ዕድል እና ጠንካራ ትስስር ይፈጥራል ብለዋል።
ለባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄው መሳካት ምሁራን ሙያዊ እገዛችንን ማጠናከር አለብን ሲሉ ተናግረዋል።
ታሪካዊ፣ ሕጋዊና ኢኮኖሚያዊ ትንተናዎችን በማዘጋጀት የኢትዮጵያን እውነተኛ ጥያቄ በዓለም አቀፍ የጥናት መድረኮችና መጽሔቶች ላይ የማቅረብ የእኛ የምሁራን ሃላፊነት በመሆኑ ይህን ልንወጣ ይገባል ብለዋል።
በተጨማሪም ዲያስፖራው የሀገሩን እውነታ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በማስረዳትና በሕዝብ ግንኙነት ሥራዎች ላይ በንቃት በመሳተፍ የዜግነት ድርሻውን ሊወጣ ይገባል ሲሉ ነው የገለጹት።
የብዙሀን መገናኛዎችም አጀንዳውን በቋሚነትና ስልታዊ በሆነ መልኩ በማስኬድ ማኅበረሰቡን ከማንቃት ባለፈ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚሆኑ ይዘቶችን ማቅረብ ላይ እንዲተጉ አስገንዝበዋል።
ይህም ለስኬቱ ተደማሪ አቅም እንደሚሆን ምሁራኑ ተናግረዋል።