የግብርና ልማት ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
የግብርና ልማት ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል
ዱራሜ ፤ጥቅምት 10/2019 (ኢዜአ)፦ በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ አሰራርና የተቀናጀ የግብርና ልማት ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥና ከተረጅነት የመውጣት ተግባር ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የትምጌታ አስራት (ዶ/ር) ገለጹ።
"የተቀናጀ ግብርና ትጋት ለተመጣጠነ ምርታማነት" በሚል መሪ ሃሳብ የበጋ ወቅት የተቀናጀ የግብርና ልማት ስራዎች የንቅናቄ መድረክ በዱራሜ ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርእሰ መስተዳድር የትምጌታ አስራት (ዶ/ር)፤ በክልሉ በግብርና ልማት እምቅ አቅም መኖሩን አንስተው በትጋት በማልማት ውጤት ማምጣት ይገባል ብለዋል።
በክልሉ ያሉ ጸጋዎችን በአግባቡ በመለየትና በማልማት ምርታማነትን ማሳደግ ዋነኛ ግባችን ነው ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ፤ የሌማት ትሩፋት፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት እንዲሁም ሰፊ የመስኖ ልማት አቅም መኖሩን አንስተዋል።
በመሆኑም በክልሉ ዘመናዊ አሰራርና የተቀናጀ የግብርና ልማት ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥና ከተረጅነት የመውጣት ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በዘርፉ ተጨባጭ ውጤት ለማስመዝገብ የሚረዱ የምርጥ ዘር፣ የማዳበሪያና ሌሎችንም የግብአት አቅርቦቶች የማሟላት ስራም ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
አቅርቦትን ጨምሮ ሌሎች ምቹ ሁኔታዎች በመፍጠር አመራሩ የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣም አሳስበዋል፡፡
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ሀላፊ ኡስማን ሱሩር፤ በክልሉ በበጋ የመስኖ ልማት ብቻ ከ149 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በማልማት ከ38 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በተለያዩ የሰብል ምርቶች፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት፣ በእንሰት፣ በቡና እና ሌሎችም ምርታማነትን የማሳደግ ጥረት ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።