ቀጥታ፡

የመንግስት እርምጃ እና የትግራይ ክልል ህዝብ አዲስ ተስፋ

በወልደሚካኤል ገብረመድህን (ኢዜአ)

ህገ ወጡ የህወሓት ቡድን የሰላም በሮችን በመዝጋት፣ ወጣቶችን በግዳጅ በማሰለፍ ሥልጣኑን ለማስጠበቅ ሕገ መንግሥታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ድርጊት በተደጋጋሚ ፈፅሟል። በተደጋጋሚ በሚሰራቸው የማይታረሙ ስህተቶች የሰው ሕይወት ተቀጥፏል፤ ለዓመታት የተገነባ መሰረተ ልማት ወድሟል። እንዲሁም ታዳጊዎችና ወጣቶች ትምህርት እንዳይማሩ አድርጓል።

በተደጋጋሚ በሚፈጽማቸው እኩይ ተግባራትና ለባዕድ ፍላጎት ተላላኪ በመሆን ሕገ መንግሥታዊ ስርዓቱን በኃይል ለማፍረስ ሞክሯል። የፌዴራል መንግሥትን በኃይል በመጣል የባዕዳን ተልዕኮን ለማሳካት የሚያደርገው ጥረት የባንዳነቱን ጥግ ከማሳየቱም በላይ ለትግራይ ክልል ህዝብ አንዳች ተቆርቋሪነት እንደሌለው በተግባር አረጋግጧል። 

“ህወሓት ቅንጣት ያህል የትግራዋይነት ባህርይ የለውም” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የገለጹት ሀሳብ የቡድኑን ባንዳነት በግልጽ ያመላክታል። የዚህ ቡድን እኩይነት በግልጽ የተገለጠው መላው ኢትዮጵያውያን በጉልበታቸው፣ በገንዘባቸውና በእውቀታቸው የገነቡትን ታላቁ ህዳሴ ግድብ አብዝተው ከሚቃወሙ እንዲሁም በቀይ ባሕር አካባቢ ያላትን አገራዊ ጥቅም አደጋ ላይ በሚጥሉ እንደ ግብጽ ያሉ የውጭ ኃይሎች ፍላጎትን በማስፈጸም፣ አገሪቷን ደካማና ጥገኛ አድርጎ ለማስቀረት በፈጸመው ተግባር ነው።

ህገወጡ ሕወሓት ተደጋጋሚ ግጭቶችን በማወጅ የትግራይ ህዝብ ለከፋ አደጋ እንዲጋለጥ አድርጓል። የሀገርና የህዝብ ሃብት ለተወሰኑ የቡድኑ አባላት የግል ጥቅም ከማዋል የተረፈውን ለእኩይ ተልዕኮው ለጥፋት ሲጠቀምበትም ቆይቷል።  በርግጥም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)  እንዳሉት የትግራይ ሕዝብ በህወሓት ምክንያት እጅግ ብዙ ዋጋ ከፍሏል።

በፌዴራል መንግሥት የተሰጠውን ተደጋጋሚ የሰላም ዕድልና አማራጭ ወደ ጎን በማለት ግጭትን የመረጠ ቡድን ነው። በመጨረሻም መንግስት በወሰደው ህግ ማስከበር እርምጃ እና በሰላም ወዳዱ የክልሉ ህዝብ ተጋድሎ አሁን ላይ ህልውናው አብቅቷል። የፌዴራል መንግሥት የአገርን አንድነት እና ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ በክልሉም ዘላቂ ሰላምና ልማት እንዲሁም ሁለንተናዊ ብልፅግና እውን ለማድረግ የተቀናጀ ስራ እያከናወነ ነው።

የትግራይ ህዝብ ህገ ወጡን ቡድን በመቃወም እና የፌደፌራል መንግስት የወሰደውን እርምጃ በመደገፍ አደባባይ ወጥቶ ጥሪውን እያሰማ ነው። ሕዝቡ ለሰላም ዋጋ መሰጠት አለበት በማለት በአደባባይ ድምጹን እያሰማ ነው። የከተማ ነዋሪዎች የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በማውለብለብ ደስታቸውን እየገለፁ ነው። በክልሉ ከተሞች ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ ተመልሰዋል።


 

ህገወጡ ቡድን ባወጣው አፋኝ ህግና ሲፈፅመው በነበረ አፈሳ ስጋት ምክንያት ተሸሽገው የቆዩ የትግራይ ክልል ወጣቶች ዛሬ በነፃነት በየከተማቸው ውስጥ እየተንቀሳቀሱ የሰላም አየር እየተነፈሱ ይገኛሉ። በአጠቃላይ ህዝቡ የለውጥ፣ የሰላምና የነፃነት አዲስ ምዕራፍ አዲስ ተስፋ ሰንቋል። መቼውንም ቢሆን በኢትዮጵያዊነቱ እንደማይደራደር ለኢትዮጵያ አንድነት ከፌዴራል መንግስት ጎን መሆኑ በተግባር በአደባባይ አሳይቷል።

በትግራይ ክልል ሰላምና ህግን እንዲሁም መረጋጋትን ለማስፈን የተጀመሩ ስራዎችን ለማጠናከር የፌዴራል መንግሥት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 62(9) እና በአዋጅ ቁጥር 359/1995 መሠረት የክልል ባለአደራ አስተዳደር አቋቁሟል። በትግራይ ክልል የተዋቀረው የፌዴራል መንግሥት ባለአደራ አስተዳደር ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት ትግራይን ያስተዳድራል።

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) ሊቀ መንበር አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር)  ባለአደራ አስተዳደር መቋቋሙን አስመልክቶ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ “የክልሉን ህዝብ ሰላምና ልማት በዘላቂነት ለማስጠበቅ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል” በማለት በመግለጽ አጽንኦት ሰጥተውታል። ይህም ሕዝቡ ለዓመታት ሲያሰቃየው ከነበረው እኩይ ባንዳ ተላቆ ሰላሙን ያረጋግጣል ማለት ነው።  

ይሄው ከፌዴራል መንግስት ከሚሰጠው አቅጣጫ ሥራውን የሚያከናውነው ባለአደራ አስተዳደር ለትግራይ ህዝብ የተስፋ ብርሃን ለማብራት ግዙፍ ሃላፊነት ተሰጥቶታል። የፌዴራል መንግስት በክልሉ ሁለንተናዊ ለውጥ እንዲመዘገብ ለሰጠው ትኩረት አድናቆታቸው የገለጹት የትዴፓ ሊቀ መንበር አረጋዊ (ዶ/ር)፤ ባለአደራ አስተዳደሩ የትግራይ ክልልን ህዝብ ሰላምና ልማት በዘላቂነት ለማስጠበቅ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለዋል።

የባለአደራ አስተዳደር አባላትም የትግራይ ክልል ህዝብን ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ ስራቸውን በታታሪነት በመከወን ሀላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የጠየቁት በክልሉና በሕዝቡ ከደረሰው ግፍ አኳያ ቀጣዩ ሀገራዊ ሃላፊነት ትልቅ መሆኑን አጽንኦት ለመስጠት ነው። በእነዚህ ጊዜያት ሰላምና መረጋጋት ማስፈን፣ የጸጥታ መዋቅሩን እንደ አዲስ ማደራጀት፣ የመንግሥት መዋቅሮችን መልሶ መዘርጋት፣ መሠረተ ልማቶችን መጠገንና ማልማት፣ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው መመለስ፣ ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ማስቀጠል፣ የሕዝቡን ሥነ ልቦና ማስተካከል፣ የሚዲያና የሕዝብ መድረኮችን ማስተባበር እንዲሁም አካታች የምርጫ ዝግጅት በማድረግ ነጻና ግልጽ ምርጫ ለማካሄድ ሁኔታ ማመቻቸት የመሳሰሉ ስራዎችን ያከናውናል።

በባለአደራው አስተዳደር የመቐለ ከንቲባ ሆነው የተሾሙት ሽሻይ አማረ (ዶ/ር) በፌዴራል መንግስት የተሰጣችውን አደራ ሲገልጹ የህገ ወጡ ህወሃት ቡድን የጥፋት እና የቁማር ፖለቲካ ለመጨረሻ ጊዜ አብቅቷል ። የተቋቋመው ባለአደራ አስተዳደር ዋና እና ቀዳሚ ተግባሩ ሰላምና መረጋጋት በማስፈን መሰረታዊ የህዝብ አገልግሎቶችና መሰረተ ልማት ስራዎችን ማጠናከር መሆኑን ጠቁመው፤ ይህን ተግባር በብቃት ለመወጣት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።


 

ከንቲባው አክለውም ለቀጣይ ምርጫ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ትኩረት እንደሚሰጠው ገልጸው፤የፌዴራል መንግስት ባለአደራ አስተዳደር ተልዕኮውን ለመፈፀም ከህዝቡ ከሲቪክ ማህበራትና ከሚመለከታቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመተባበር እንደሚሰሩም  አረጋግጠዋል።

በክልሉ በህዝብ የተመረጠ ክልላዊ መንግስት እስከሚመሰረት ድረስ የፌዴራል መንግስት የክልሉን ሁለንተናዊ ሰላም ለማረጋግጥና የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማስፋት ፈጣንና ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ ይገኛል።

በሕገ ወጡ ህወሓት የተቋረጡ መሰረተ ልማቶችና ማህበራዊ አገልግሎቶች እንዲቀጥሉ፣ ወደ ክልሉ መድኃኒትና እርዳታ እንዲገባ ማድረግ እና ሰላምና መረጋጋትን ማስቀጠል የመሳሰሉ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ለአብነት ማንሳት ይቻላል። በፌዴራል መንግስት በክልሉ ህግና ሰላም ለማስፈን፣ የህዝብ ማህበራዊ አገልግሎቶችን ለማስቀጠል እየተደረገ ያለው ጥረት መንግስት ለህዝቡ ሰላምና ልማት እንዲሁም እንክብካቤ ያለውን ከፍተኛ ፍላጎትና ቁርጠኝነት በግልጽ ያሳያል።

የፌዴራል መንግሥት ባለአደራ አስተዳደር የተሰጠውን ተልዕኮ ለማሳካት የሁሉም አካላት በተለይ የትግራይ ህዝብ፣ የትግራይ ምሁራን፣ ፖለቲከኞች እና ሲቪክ ማህበራት ድጋፍ፣ ዝግጁነትና ትብብር ወሳኝ ነው።

በትግራይ ሰማይ ስር የጽኑ ሰላም መባቻ እና የብልፅግና ጉዞ ፀሐዩ ሲወጣ የችግር ደመና ተገፎ የእውነትና የነፃነት ብርሃን እየፈነጠቀ ነው። ህዝቡ ለዘመናት ለሰላም፣ ለአንድነት፣ ለፍትህና ለእኩልነት የከፈለው ከፍተኛ ዋጋ እና ያነገበው ፍላጎት እውን ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም